የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ እንደ ሀገር ለተጀመረው ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ለውጥ የማይተካ ሚና እንዳለው ተገለፀ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ፈጣን ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻል የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታውቋል።
”ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉ ዓቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ( March 8 ) በዓል በወረዳው ተከብሮ ውሏል፡፡
በዓለም ደረጃ ለ114ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ በወረዳ ደረጃ በተከበረው ዓለም ዓቀፉ የሴቶች ቀን የወረዳው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሴት መንግስት ሰራተኞች፣ የወረዳው ሁሉም ቀበሌዎች ተወካዮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል፡፡
የወረዳው ሴቶችና ህፃናት ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ወይዘሮ የምስራች ከፊያለው በወረዳው ሴቶች በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎና እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ርብርብ አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም በሀገር ደረጃ በለውጡ መንግስት የተያዙ ዕቅዶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ተፈፃሚ እንዲሆኑ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊዋ፥ መንግስት ያመቻቸላቸውን ዕድል በመጠቀም ሴቶች በሁሉም ረገድ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆን መቻል እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡
በዕለቱ የወረዳው ሴቶች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠቃለያ ድጋፍ ለማድረግ የቦንድ ግዢ የፈፀሙ ሲሆን ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት መተባበር ለራስ ተጠቃሚነት የሚደረግ የሁሉም ግዴታ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ እንደ ሀገር ለተጀመረው ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ለውጥ የማይተካ ሚና እንዳለው ተገለፀ

More Stories
በሩብ ዓመቱ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለመጀመሪያ ዙር ያሰለጠናቸውን ምልምሎች እያስመረቀ ነው
የፍትህ አስተዳድር ስርዓቱ ብቃትንና ሥነ-ምግባርን መሰረት ያደረገ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፍትህ ቢሮ አሳሰበ