ሴቶች በእውቀትና በሀሳብ በመደጋገፍ ራሳቸውን ለማብቃት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ተጠቆመ

ሴቶች በእውቀትና በሀሳብ በመደጋገፍ ራሳቸውን ለማብቃት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሴቶች በእውቀትና ሀሳብ በመገነባባትና መደጋገፍ ራሳቸውን ለማብቃት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ልክነሽ ስርገማ ገለፁ፡፡

በክልሉ የወልቂጤ ክላስተር ሴት የመንግስት ሰራተኞች አለም አቀፍ የሴቶች ቀን “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል!” በሚል መሪ በፓናል ውይይትና በልዩ ልዩ ሁነቶች በወልቂጤ ከተማ አክብረዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ልክነሽ ስርገማ በዚህ ወቅት እንደገለፁት ሴቶች ከዚህ ቀደም ይደርስባቸው የነበሩ ፈተናዎችንና ጫናዎችን በማለፍ ዛሬ ላይ እንደ ሀገር የተሻለ አቅም በመፍጠርና ያላቸው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በማህበሰረሰብና በሀገር ግንባታ እንዲሁም ትውልድን ለማጽናት ያላቸው ድርሻ የጎላ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም ሴቶች እርስ በርስ ከመጠላለፍና ከመተቻቸት በመራቅ በእውቀትና በሀሳብ መገነባባትና መደጋገፍ እንደሚገባ ጠቁመው፥ ሴቶች ራሳቸውን ለማብቃት በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ሴቶች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመሰማራትና ጠንክሮ በመስራት ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውም ወ/ሮ ልክነሽ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ የወልቂጤ ክላስተር ህብረት ሰብሳቢና የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ የስርዓተ ፆታ አስተባባሪ ወ/ሮ ህይወት ተከተል በበኩላቸው ሴቶች ራሳቸውን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ በትብብርና በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፥ በተለይ በራሳቸው ላይ ያላቸውን የእንችላለን አስተሳሰብ ማጎልበትና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም በክልሉ በሚከናወኑ ልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊ ሴቶች መካከል ወ/ሮ አሰለፈች ሀይሌ፣ ወ/ሮ ብርቱካን እንጁሉና ወ/ሮ ሜሮን ታደሰ በሰጡት አስተያየት ሴቶች ዕድሉን ካገኙ የማይችሉት ስራ እንደሌለ ጠቁመው፥ ራሳቸውን ለማብቃትና ለማጎልበት በርትተው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በክልሉ ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በውሳኔ ሰጪነት ከማብቃት አንጻር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አበረታች በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በዓሉ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ114ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ49ኛ ጊዜ እንዲሁም በክልሉ ለ2ኛ ጊዜ በመከበር ላይ የሚገኘው የሴቶች ቀን በዓል፥ የወልቂጤ ክላስተር ሴት የመንግስት ሰራተኞች “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል!” በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይትና በልዩ ልዩ ሁነቶች በከተማው አክብረዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን