የአካባቢን ፀጋ መሠረት ያደረጉ የክህሎት ስልጠናዎች ተነሳሽነት ያለው ስራ ፈጣሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያግዝ ተገለጸ

የአካባቢን ፀጋ መሠረት ያደረጉ የክህሎት ስልጠናዎች ተነሳሽነት ያለው ስራ ፈጣሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያግዝ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአካባቢን ፀጋ መሠረት ያደረጉ የክህሎት ስልጠናዎች ተነሳሽነት ያለው ስራ ፈጣሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያግዝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር ብቁና ተነሳሽነት ያለውን ስራ ፈጣሪ ዜጋን ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል።

የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ፀጋ መሠረት ያደረገ የስራ እድል ፈጠራ ተግባራት ቢከናወኑም ብቁና ተነሳሽነት ያላቸው ስራ ፈጣሪ ዜጎች ያስፈልጋሉ።

ይህን መሠረት ያደረጉ ተግባራት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በኩል እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ በአርባምንጭ ከተማ ባካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ብቃትና ክህሎት ያለውን የሰው ሃይል በክልሉ ለመፍጠር የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት የተሰጣቸውን ሀገራዊ አደራ አሟጠው ሊወጡ ይገባል።

የክልሉን እምቅ ፀጋ በመጠቀም ወጣቱን በእውቀት በማደራጀት ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ጊዜ የማይሰጠው ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እውቀትን መንዝሮ መጠቀም ያሻልም ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ በበኩላቸው፤ የውጪ ስራ ስምሪት ጋር ተያይዞ በክልሉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከተሞች ሊፈቱ ይገባል ብለዋል።

በአጫጭርና ረጃጅም ስልጠናዎች ረገድ ኮሌጆች ያሉባቸውን መጠነ ሰፊ ችግር ሊፈቱ ይገባል ያሉት አቶ አብዮት፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በማህበር ተደራጅተው የሚሰሩ ወጣቶችን በዘርፉ ያላቸውን እውቀት እየመዘኑ ማለፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

ዘጋቢ: በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን