በትምህርት ዘርፍ ለሚስተዋለው የጥራት ችግር አጠቃላይ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራምን በፍትሀዊነት መተግበር እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በትምህርት ዘርፍ ለሚስተዋለው የጥራት ችግር አጠቃላይ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራምን በፍትሀዊነት መተግበር ይገባል ሲል የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

የአጠቃላይ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም የማጠናቀቂያ ግምገማና የክልል ትምህርት ቢሮዎች የልምድ ልውውጥ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

የአጠቃላይ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም በአለም ባንክ ድጋፍ በሀገሪቱ በሚገኙ ክልሎች እየተተገበረ መቆየቱ ይታወቃል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ በመድረኩ መክፈቻ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት በክልሉ በትምህርት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለቅሞ በመፍታት ረገድ ስራዎች መጀመራቸውን አመላክተዋል።

ይበልጥ በበምህራንና በትምህርት ጥራት ዙሪያ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች መፍትሄ ያገኙ ዘንድ መጠነ ሰፊ ስራዎች መጀመራቸውን አውስተው ለዚህ ስኬት ባለድርሻ አካላት እገዛ ሊያደርጉ ይገባልም ብለዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ይበልጣል አያሌው በበኩላቸው በክልሉ ከ26 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገው አጠቃላይ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም የተፈለገውን ውጤት የተመዘገበ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በሀገሪቱ በሚገኙ ክልሎች ከ45 ሺህ በላይ ት/ቤቶች በዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸውን ያነሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው ለዚህም የአለም ባንክ ከሀገሪቱ መንግስት ጋር ያደረገው ጥረት ከፍተኛ ነውም ብለዋል።

በመድረኩ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።

ዘጋቢ፡ በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን