አጋር ድርጅቶች ለጤና ሥርዓት መሻሻልና ልምድ ልውውጥ የላቀ ሚና አላቸው

ሀዋሳ፡ መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጤና ዘርፍ የሚሰሩ አጋር ድርጅቶች ለማህበረሰቡ ከሚሰጡት ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች በተጨማሪ የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻልና ለባለሙያው ልምድ መቅሰሚያ እየሆነ እንዳለ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

ጆይስ ቮይስ ሚኒስትሪ ኢንተርናሽናል የተሠኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኣሪ ዞን ቢተማል ጤና ጣቢያ ለ5 ተከታታይ ቀናት የነፃ ህክምና ሰጥቷል።

መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተለያዩ የልማትና ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ በመሣተፍ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር የመንግስትን የልማት አቅም በመደገፍም የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ጆይስ ቮይስ ሚኒስትሪ ኢንተርናሽናል የተሠኘ ግብረሠናይ ድርጅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኣሪ ዞን ቢተማል ጤና ጣቢያ ለአምስት ቀናት ልዩ ልዩ ህክምና ከመስጠቱም በተጨማሪ የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ለጤና ጣቢያው ድጋፍ አድርጓል።

የህክምና አሰጣጡን የተመለከቱት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ እንደገለፁት፤ በጤና ዘርፍ የሚሰሩ አጋር ድርጅቶች ከማህበራዊ አገልግሎታቸው ባሻገር የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻልና ለባለሙያው የክህሎት ማሸጋገሪያም ነው።

ድርጅቱ ከህክምና አገልግሎቱ በተጨማሪ በድጋፍ የሰጡትን ቁሳቁስ በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚገባ ያሳሰቡት ኃላፊው ድርጅቱ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

የኣሪ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የዞኑ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ፤ ድርጅቱ ከህክምና አገልግሎት በተጨማሪ ስላደረገው የግብዓትና ክህሎት ድጋፍ አመስግነዋል።

የኣሪ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ይሁን ጋሎ፤ በድጋፍ የተገኙ ግበዓቶችን ተቋሙ ለታለመለት ዓላማ እንዲያውል አስፈላጊው ክትትልና እገዛ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

የጆይስ ቮይስ ሚኒስትሪ ኢንተርናሽናል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አዳነ በራሳ፤ ድርጅቱ ላለፉት 25 አመታት በመላው ኢትዮጵያ ህክምናውን ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው፤ ሠሞኑን በኣሪ ዞን ሲካሄደ በነበረው ህክምና ከዘጠኝ ሺህ በላይ ሰዎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አረጋግጠዋል።

ከነፃ ህክምናው የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ባለሙያዎች መሣተፋቸውንና ከህክምናው በተጓዳኝ ልዩ ልዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ለጤና ጣቢያው ድጋፍ ማድረጋቸውን አመላክተዋል።

በነፃ ህክምናው ተጠቃሚ የሆኑት አካላትም ስለተደረገላቸው መልካምነት ድርጅቱንና ያስተባበሩትን የመንግስት አካላት አመስግነዋል።

ዘጋቢ፡ መልካሙ ቡርዝዳቦ – ከጂንካ ቅርንጫፍ