የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች የህዝብን ጥያቄ ሊመልስ በሚችል መልኩ ሊሆን እንደሚገባ የሀዲያ ዞን ምክር ቤት አበላት ገለጹ

የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች የህዝብን ጥያቄ ሊመልስ በሚችል መልኩ ሊሆን እንደሚገባ የሀዲያ ዞን ምክር ቤት አበላት ገለጹ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 03/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በየደረጃው የተጀመሩ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች የህዝብን ጥያቄ ሊመልስ በሚችል መልኩ ሊሆን እንደሚገባ የሀዲያ ዞን ምክር ቤት አበላት ገለጹ።

ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው የምክር ቤቱ 4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት 24ኛ መደበኛ ጉባኤ በዞኑ በሁሉም መስኮች በተከናወኑ የአፈጻጻም ሪፖርቶች ላይ በመምከር ተጠናቋል።

የሀዲያ ዞን ምክር ቤት የ4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት 24ኛ መደበኛ ጉባኤ በዞኑ በሁሉም መስኮች የተከናወኑ አፈጻጸሞችን በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።

የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉበኤ ወ/ሮ እቴነሽ ሙሉጌታ የምክር ቤት አባላት በዞኑ ሁሉም መስኮች በ6 ወራት የተከናወኑ የአፈጻጸም ሪፖርቶችን የገመገሙበትና በጠንካራና ደካማ ጎኖች የተነሱ አፈጻጸሞችን በመለየት የቀጣይ ጊዜ አቅጣጫ ያስቀመጡበት እንደሆነም ተናግረዋል።

የሚቀርቡ ሪፖርቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎችን እያሳዩ መሆኑን የገለጹት ዋና አፈ-ጉባኤዋ የተገኙ ተጨባጭ ለውጦችን ለማስቀጠል የድጋፍና ክትትል እንዲሁም የቅንጅት ስራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

በዞኑ አስተዳደር ምክር ቤትና በአስፈጻሚ ምክር ቤት የተከናወኑ የ6 ወር የአፈጻጸም ሪፖርች በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ በአቶ ማቲዎስ አኒዮ እና በምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤዋ በወ/ሮ አምነሽ ክፍሌ በኩል በዝርዝር ቀርቧል።

በዚህም በግብርና፣ በጤና፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በፀጥታ፣ በትምህርትና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት በዝርዝር የቀረበ ሲሆን በውሃ፣ በከተማ ልማት፣ በትራንስፖርትና በሌሎችም ዘርፎች የተከናወኑ አፈጻጻም ሪፖርቶች በስፋት ተዳሷል።

በዚህም በግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ከመደበኛ የእርሻ ስራ በተጨማሪ ለመስኖ ልማት በተሰጠው ልዩ ትኩረት 269ሺህ 963 አርሶ አደሮችን ለማሰልጠን ታቅዶ 218ሺህ 240 አርሶ አደሮችን ማሰልጠን መቻሉን አንስተዋል።

በጤናው ዘርፍ እንደ ዞን በተሰራው ስራ 83ሺህ 580 የቤተሰብ ሙሉ ፓኬጅ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ 72ሺህ 360 ቤተሰብን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በሪፖርቱ የተነሳ ሲሆን በተለይ የእናቶችንና ህጻናትን ሞት የመቀነስ ስራም ትኩረት የተሰጠበት መሆኑን በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በኦዲት ግኝት ክትትልና አመላለስ፣ በአፈር ማዳበሪና ምርጥ ዘር አቅርቦት፣ በአጠቃላይ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በህግና ፍትህ ጉዳዮች በ6ወራት ውስጥ የተከናወኑ ጠንካራና ደካማ አፈጻጸሞች ተለይቶ ለምክር ቤቱ በዝርዝር ቀርባዋል።

በፌዴራልና ክልል ደረጃ ያሉ የምክር ቤቱ አባላት የተሳተፉበት ጉባኤ እንደሆነ የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪ ምክር ቤቱ ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በስፋት የመከረበት መሆኑን ዋና አስተዳሪው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የሀዲያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ6 ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት በፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ዳኛ ጥላሁን ዴታሞ በኩል የቀረበ ሲሆን በ6ወር አፈጻጻም በወንጀልና በፍትሐብሔር መዝገቦች ከታቀደው 92 ከመቶ በማሳካት ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመዋል።

ሆኖም ከተዘዋዋሪ ችሎት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ዝቅተኛ አፈጻጻም መመዝገቡን በሪፖርታቸው ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፥ የበጀትና ተያያዥ ጉዳዮች ችግር ለክፍተቱ መፈጠር በመንስኤነት አቅርበዋል።

የምክር ቤቱ አባለት የቀረቡ ሪፖርቶችን መነሻ በማድረግ በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ አፈጻጻሞች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

አንድ አንድ የምክርቤት ቤት አባለት በሰጡት አስተያየት እንደዞን በሁሉም መስኮች የተጀመሩ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች የህብረተሰቡን ጥያቄ ሊመልስ በሚችል መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ በአቶ ማቲዎስ አኒዮ በኩል በዕጩነት የቀረቡ የተለያዩ ሹመቶችን ተቀብሎ ያጸደቀ ሲሆን፥ በዚህም መሠረት አቶ ሰሙኤል ሽጉጤ ዋና የመንግስት ተጠሪና የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ፣ አቶ ማሳይ ተፈሪ ረደት የመንግስት ተጠሪ እንዲሁም የ3 መምሪያ ኃላፊዎችንና የ6 ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶችን ሹመት ተቀብሎ በማጽደቅ ተጠናቋል።

ዘጋቢ: አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን