በመንግስት እየተመቻቸ የሚገኘዉን የዉጭ ሀገር የስራ ስምሪት እድል ህብረተሰቡ በአግባቡ ሊጠቀም እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስራና ክህሎት ቢሮ ጥሪ አቀረበ።
ይህም በህገ-ወጥ መንገድ ለስራ ፍለጋ ከሀገር የሚወጡ ዜጎች ላይ የሚደርሰዉን በደሎችና የመብት ጥሰቶችን የሚያስቀር መሆኑም ተጠቁሟል።
የዉጭ ሀገር የስራ ስምሪት መንግስት ሰራተኛ ከሚፈልጉ ሀገራት ጋር ህጋዊ ስምምነት በመፈፀም ክህሎት ያላቸዉ ዜጎች ደህንነታቸዉ ተጠብቆ ወደ ዉጭ ሀገር በመሄድ የስራ ዕድል የሚጠቀሙበት አሰራር መሆኑን የቢሮዉ ምክትል ሀላፊና የአሰሪና ሰራተኛ ዘርፍ ሀላፊ ዶክተር ተክለአብ ቡሎ ተናግረዋል።
ይህም ከዚህ ቀደም ዜጎች ለስራ ፍለጋ በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር በሚወጡበት ወቅት ይደርስባቸዉ የነበሩ በደሎችንና የመብት ጥሰቶችን የሚያስቀር በመሆኑ ዜጎች በአግባቡ መጠቀም እንደሚጠበቅባቸዉ ዶክተር ተክለዓብ አስገንዝበዋል።
በክልሉ በዚህ ዓመት ወደ 24 ሺህ የሚጠጎ ዜጎችን የተለያዩ የክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት የዉጪ ሀገር ስራ ስምሪት ለመስጠት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አንስተዉ፤ ከዚህም በእስካሁኑ 3 ሺህ 710 ዜጎች ብቻ መስፈርቱን አሟልተዉ በተለያዩ ሀገራት በመሄድ ስራ መጀመራቸዉን ጠቁመዋል።
ስልጠና ጨርሰዉ በተለያዩ ምክንያቶች የዘገዩ 360 ወጣቶች በሂደት ላይ የሚገኙ ወጣቶች መኖራቸዉን የተናገሩት ዶ/ር ተክለዓብ፤ አፈፃፀሙ ከተያዘዉ ዕቅድ አንፃር በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ይህን ለማሻሻል በየደረጃዉ የሚገኙ አካላት ኃላፊነታቸዉን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ያጠናቀቁና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ያላቸዉ ዜጎች በእነዚህ ኮሌጆች ሙሉ መረጃ በአንድ ማዕከል ከተመዘገቡ በኋላ የክህሎት ስልጠና በመዉሰድ የእድሉ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
የህገ-ወጥ ደላሎች በሂደቱ መሳተፍ ስራዉ የተፈለገዉን ያክል ዉጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት መሆኑን ጠቁመዉ፤ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እነዚህ አካላትን ከመስመር የማስወጣት ስራ እየተሰራ ነዉ ብለዋል።
የዉጭ ሀገር የስራ ስምሪት አብዛኛዉ ጉዳይ ያለክፍያ የሚፈፀም በመሆኑ ከፍተኛ ገንዘብ ያስፈልጋል በሚል ለሚሰራጩ አሉባልታዎች ቦታ ባለመስጠት ወጣቶች የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
በክልሉ ቦንጋ፣ ሚዛን፣ ቴፒና ተርጫ ፖሊ ቴክኒክና ጪዳ ኢንዱስትሪያል ኮሌጆች የዉጭ ሀገር የስራ ስምሪት ስልጠና እንዲሰጡ በስራና ክህሎት ሚኒስቴርና በክልሉ መንግስት እዉቅና ተሰጥቷቸዉ በስራ ላይ እንደሚገኙም ዶ/ር ተክለአብ ቡሎ አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡ በአሰግድ ሣህሌ – ቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ መጋቢት 04/2017 ዓ.ም
አጋር ድርጅቶች ለጤና ሥርዓት መሻሻልና ልምድ ልውውጥ የላቀ ሚና አላቸው
የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች የህዝብን ጥያቄ ሊመልስ በሚችል መልኩ ሊሆን እንደሚገባ የሀዲያ ዞን ምክር ቤት አበላት ገለጹ