በዞኑ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን የምክር ቤት አባላት መመልከታቸው ስራው እንዲፋጠን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ያስችላል ተባለ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 02/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዞኑ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን የምክር ቤት አባላት ተዘዋውረው መመልከታቸው ህዝቡ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ከማረጋገጣቸው በተጨማሪ ስራውን እንዲፋጠን የበኩላቸው ሚና እንዲወጡ ያስችላቸዋል ሲል የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር ገለፀ።

የዞኑ ምክርቤት አባላት በዞኑ እየተሰሩ ያሉትን ሀገራዊና ዞናዊ የልማት ስራዎችን ተመልክተዋል።

የዞኑ ምክርቤት 4ኛ አመት 12ኛ ዙር 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።

የምክርቤቱ አባላት በነበራቸው ጉበኝት በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለትን የደንቢ ሎጅ የግንባታ ሂደት ያለበትን ደረጃ የተመለከቱ ሲሆን፥ የሎጁ ግንባታ ፕሮጀክት አስተባባሪ ጋሻው ዳዊት ስራው ከ93 በመቶ በላይ መድረሱንና ለምርቃት መቃረቡን ገልፀዋል።

የሎጁ መገንባት አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ከማድረጉ በተጨማሪ ለአካባቢ ወጣቶቾም የስራ እድል ይፈጥርላቸዋል ብለዋል።

ሀይቁ እንዳይበከል እና የአካባቢው ስነ-ምህዳር ከመጠበቅ አንፃር ያለውን ጉዳይ በተመለከተ የምክር ቤቱ አባላት ላነሱት ጥያቄ የስራ ሀላፊዎቹ ምላሽ ሰጥተዋል።

ሌላው የጉብኝቱ አካል ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመሠረት ዶንጋይ ያስቀመጡለት የሚዛን አማን አለማቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሲሆን የስራው አፈፃፀም 75 በመቶ ላይ መድረሱን የሳምሶን ቸርነት ተቋራጭ ስራ የአየር መንገዱ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢዮብ ሞላ ገለፀዋል።

ስራው እንዳይፋጠን የወሰን ማስከበር እና የአካባቢው የአየር ሁኔታ ተፅኖ ማሣደሩን ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪው አቶ ሀብታሙ ካፕቲን ለአየር መንገዱ ግንባታ እውን መሆን ከአካባቢው የተነሱ ነዋሪዎች ያላቸው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተው እስከ አሁን ለልማት ተነሺዎች ዞኑ ከ150 ሚሊዮን ብር ካሣ መክፈሉን ተናግረዋል።

ከዚህ ቦታ ለሚነሱ ነዋሪዎች ማህበራዊ መሠረታቸው እንዳይናጋ በአንድ አካባቢ ለማስፈር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በዞኑ ከሚከናወኑ የልማት ስራዎች አንዱ የሆነ የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማት የጉብኝቱ አካል ሲሆን ስራው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደርሩ ከንቲባ አቶ ግሩም ተማም ተናገረዋል።.

የዞኑ ዋና አስተዳደሪ በአካቢው እተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የምክር አባላቱ መመልከታቸው ህዝቡን የልማት ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ከማረጋገጣቸው በላይ የሚሰሩ ስራዎች እንዲፋጠን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ያስችላቸዋል ብለዋል።

በጉብኝቱ ከምክር ቤቱ አባላት በተጨማሪ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አፈ ጉባኤ ወንድሙ ኩርታን ጨምሮ የወረዳና የዞን መስሪያ ቤቶች አስፈፃሚዎችና ፈፃሚዎች ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።

ዘጋቢ፡ ብዙአየሁ አሣሣኸኝ – ከሚዛን ጣቢያችን