ለኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት የሆነውን የቁጠባ ባህል ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 02/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሁሉም የወረዳው ነዋሪዎች ካላቸው ላይ በመቆጠብ ለኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት የሆነውን የቁጠባ ባህል ማሳደግ እንደሚገባ በጌዴኦ ዞን የዲላ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ገለጸ።

የወረዳው ህብረት ሥራ ልማት ጽ/ቤት ‘ጉምንሶ ህብረት ሥራ ማህበር’ ምስረታና የቁጠባ ማሰባሰቢያ መድረክ አካሂዷል፡፡

“ጉምንሶ” የተሰኘ ህብረት ሥራ ማህበር ምስረታና የቁጠባ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በጌዴኦ ዞን የዲላ ዙሪያ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ቦኮ የህብረት ሥራ ማህበራት የህብረተሰቡ ኢኮኖሚ መሠረት መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም በወረዳው 21 የሚሆኑ ህብረት ሥራ ማህበራት እንደነበሩ በመጠቆም የህብረት ሥራ ማህበራትን ማቋቋሚያ ሪፎርም በማድረግ ጉምንሶ የህብረት ሥራ ማህበር በማቋቋም በንቅናቄ ቁጠባ የመሰብሰብ ሂደት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ወረዳው ቡና፣ እንሰት እና የተለያዩ የግብርና ምርቶች የሚመረትበት ወረዳ መሆኑን በመጠቆም አርሶአደሩ ማህበረሰብ ሆነ ሁሉም የወረዳው ነዋሪዎች ካላቸው በመቆጠብ ለኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት የሆነውን የቁጠባ ባህል ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የወረዳው ህብረት ሥራ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደመቀ ገመደ በበኩላቸው እንደ ሀገርም የህብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም የተጀመረ በመሆኑ እንደ ወረዳ ጉምንሶ የተሰኘ የህብረት ሥራ ማህበር በአንድ ጀንበር አንድ ሚሊዮን የቁጠባ ብር ለመሰብሰብ ግብ ጥለው እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ማህበራት በተናጠል ከመጓዝ ይልቅ ጠንካራ ህብረት መስርትው ሲንቀሳቀሱ የማህበሩ አባላትን ከመጥቀም አንጻር ያለው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ በወረዳው በአዲስ የተቋቋመውን ማህበር ለማጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደረጉ ገልጸዋል።

በምስረታ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የጌዴኦ ዞን ህብረት ሥራ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተካዬ በበኩላቸው የህብረት ልማት ሥራ ማህበር የተቋቋመለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም የነበሩ ማህበራትን ለማጠናከር በተሠራው ሪፎርም በዞኑ 10 የተጠናከረ ህብረት ሥራ በማቋቋም ከዚህ ቀደም የነበሩ የአሠራር ክፍተቶችን ለማረም መሠራቱንና ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው 12 ሚሊዮን ብር ቁጠባ እስካሁን 10 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን በመጠቆም ዕቅዱን ለማሳካት ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በምስረታውና በቁጠባ ገንዘብ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ ተገኝተው ሲቆጥቡ አግኝተን ካነጋገረናቸው መካከል አቶ ታምራት ሽብሩ እና አቶ ወንድሙ ካሳ በወረዳው የሆጥቻ እና የሽገዶ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ ቁጠባ የነገ ኑሯቸውን ለማሻሻል ያለውን ፋይዳ በመረዳት ከተረፈው ሳይሆን ካላቸው በመቆጠባቸው ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የወረዳው አመራሮች እና በወረዳው ከሚገኙ ቀበሌያት የተወጣጡ አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን