ጤና ጣቢያው ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ የተሻለ ሕክምና ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራት በተቀናጀ መልኩ እያከናወነ እንደሚገኝ የሥራ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል።
የጪዳ ጤና ጣቢያ የጪዳ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎችን ጨምሮ ከ10 በላይ ለሚሆኑ አጎራባች ቀበሌያት የፈውስ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በመሆኑም የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ ካለፉት ዓመታት ይልቅ አሁን ላይ መሻሻል መኖሩን ተገልጋዮች ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ጤና ጣቢያው ከሚሰጠው ከአገልግሎት ስፋትና ተደራሽነት አንጻር ደረጃውን ቢያሻሽል በሆስፒታል ደረጃ የሚሰጠውን ሕክምና ለማግኘት ርቀው በመሄድ የሚያባክኑትን ጊዜና ገንዘብ ማትረፍ እንደሚችሉ ተገልጋዮች ተናግረዋል።
የጤና ጣቢያው ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ገዛኸኝ በበኩላቸው፤ ጤና ጣቢያው በተሻለ ሁኔታ በሰው ኃይል የተደራጀ በመሆኑ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
እንደወረርሽኝ ሆኖ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘውን የወባ በሽታን ለመከላከል የሚያስችል ሥራ በተቀናጀ ሁኔታ ሲሠራ በመቆየቱ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።
የጪዳ ጤና ጣቢያ ለተገልጋዮች የተሻለ የፈውስ ሕክምና አገልግሎት መስጠት እንዲችል ከ10 በላይ የጤና ኬላዎች፣ ከአመያና ታርጫ ጠቅላላ ሆስፒታል ጋር በቅንጅት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
የጤና ጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም የሚታዩ ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቅረፍ የተገልጋዩን ሕብረተሰብ ፍላጎት ማርካት እየተቻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
በመሠረተ ልማት ዝርጋታና የግንባታ ሥራን በማስፋት በእናቶችና ሕጻናት የአገልግሎት አሰጣጥን በስፔሻሊስት ደረጃ ለመስጠት ታስቦ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በጪዳ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት የመንግሥት ፋይናንስ ዩኒቲ አስተባባሪ አቶ ዘውዴ ወራቦ በበኩላቸው፤ ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሣት በከተማ አስተዳደሩ ሥር ለሚገኙ የጤና ተቋማት በልዩ ሁኔታ የድጋፍ ተግባር መኖሩን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢሠራ ወረዳ ተገልጋዮች ተናገሩ
የጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ ተፈጥሯዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲቆይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አሰታወቀ
በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ እስኪጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ የሸኮ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለፁ