ሂጂራ ባንክ ሚዛን አማን ቅርንጫፍ ታላቁን የረመዳን ወርን ምክንያት በማድረግ በሚዛን አማን ከተማ በሚገኘው አዝሃር መስጂድ በመገኘት በከተማዋ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች የኢፍጣር ድጋፎች አድርጓል።
ባንኩ በዕለቱ 75 ለሚሆኑና ለችግር ለተጋለጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከ100 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ ዱቄትና ዘይት ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንትና የነስር መስጅድ ኢማም ሼህ አደም መሀመድ፤ ሂጅራ ባንክ የእስላማዊ አስተምህሮቶችን በመተግበር ለችግር የተጋሉጡትን ወገኖች መርዳቱ የሚያስመሰግነው መልካም ስራ መሆኑን ገልጸው በሌሎች ተቋማትም ጅምሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በረመዳን ጾም ወር እንዲህ ዓይነት መረዳዳትና ችግረኞችን መደገፍ የእምነቱ አስተምህሮ እና ተግባር በመሆኑ የሚያስደስት ነው ብለዋል።
በሚዛን አማን ከተማ የሚገኘው የአዝሀር መስጅድ ኢማም ሸህ መሀመድ ፈትህ እንደገለፁት፤ በእስልምና ሀይማኖት አስተምህሮ ከተቀመጡት መሰረታዊ ነጥቦች የረመዳንን ፆም መጾም፣ የተቸገሩ ወገኖችን መደገፍና መንከባከብ እንዲሁም ዘካን በአግባቡ ማውጣት ተጠቃሾች ናቸው።
የሂጅራ ባንክ የደቡብ ምዕራብ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ መሀመድ በበኩላቸው፤ ባንኩ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ለሙስሊሙ ሕብረተሰብ የሚሰጥ ሲሆን እንደሀገር በተለያዩ አካባቢዎች ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችንና አቅመ ደካሞችን እየደገፈ እንዳለ ገልጸዋል።
ባንኩ 1446ኛውን የረመዳን ፆም ምክንያት በማድረግ በሚዛን አማን ከተማ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
ድጋፉ 75 ለሚሆኑና ለችግር ለተጋለጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከ100 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ ዱቄና ዘይት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀው በቀጣይም ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል
በስነ ስርዓቱ ላይ የሀይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሂጅራ ባንክ አመራርና ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።
ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን

More Stories
የአፈር ጤናን በመጠበቅና ለምነትን በማሻሻል የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።
የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት ይሠራል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
ጥራቱ የተጠበቀ ከ500 ቶን በላይ እሸት ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ