በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችንና ማህበራዊ ጫናዎችን ለመከላከል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ የካቲት 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችንና ማህበራዊ ጫናዎችን ለመከላከል ብሎም ሐብት አፍርተው የኢኮኖሚ ባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል ቀጣይነት ያለው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለፀ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ114ኛ እንደሀገር ለ49ኛ ጊዜ የሴቶች ቀን በደቡብ ኦሞ ዞን በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወ/ሮ ዶቦ አውኖ የሴቶችን መብት የሚፈታተኑ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተወግደው ዘላቂ ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
ሁሉ አቀፍ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ቀጣይነት ባለው መልኩ ውጤት እንዲያስመዘግብ ሁሉም መረባረብ አለበት ሲሉ ምክትል አፈጉባዔዋ አሳስበዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ጎባ ኛላማ በየዓመቱ የሚከበረው የሴቶች ቀን ከማክበር ባለፋ የሚተላለፉ መልዕክቶች ወደተግባር ተቀይሮ ማየት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የሴቶች ቁጠባ ባህል እንዲዳብር፣ በሰፊው የግብርና ምርት ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ፣ በጤና፣ በንግድ እንዲሁም ሀገራዊ ሰፋፊ ልማቶች የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል።
መመሪያው ለሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃማነት ከመቸውም ጊዜ በላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ሲሉ ወ/ሮ ጎባ ገልፀዋል።
ጂንካ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የመንግስት የልማት አጋር አካላት በመድረኩ ተገኝተው ከቀኑ ጋር በተያያዘ መልዕክት አስተላልፈዋል ።
በጂንካ ዩኒቨርሲቲ በኩል ጥናታዊ ፁሑፍም ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
ቀኑ በተለያዩ ዝግጅቶችና መርሐ ግብሮች ተከብሯል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በብዝሃነት ውስጥ የሚንፀባረቁ የመረዳዳትና የአብሮነት በጎ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና የየዞን ከፍተኛ አመራሮች በሣውላ ማረሚያ ተቋም አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና ልየታ ተካሄደ