ሀዋሳ፡ የካቲት 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢፌዴሪ የፓርላማና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባላት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር በተለያዩ የልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ከጌዴኦ ዞን አጠቃላይ ሴክተር ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
ተወካዮቹ ህብረተሰቡ ለሚያነሷቸው የልማት ጥያቄዎች አፋጣኝ እልባት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ አጠቃላይ የዞኑ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ማናጅመንት አካላት በመሰረተ ልማት ዝርጋታ በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በጤና አገልግሎት አሰጣጥ፣ በመንገድ ልማትና በውሃ መሥመር ዝርጋታ፣ በመብራትና ቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት አሰጣጥ፣ ህገወጥ የነዳጅ ግብይትና በሌሎች ዘርፎችም የተስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ እልባት እንዲሰጥ የማናጅመንት አባላቱ ጥያቄ አንስተዋል፡፡
የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ(ዶ/ር) በሳምንቱ ከህዝቡ ጋር በነበራቸው ውይይትና መስክ ጉበኝት በከተማ ልማትና በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ጥሩ መነቃቃትን እንደፈጠረ ገልጸዋል።
በፌዴራል መንግስት የሚሠራው ዲላ- ቡሌ- ዋጩ መንገድ ፕሮጀክት በካሳ ክፍያ ምክንያት ሥራው እንዳይስተጓገል የዞን፣ የክልልና የፌዴራል ጉዳዩ ሚመለከታቸው አካላት አሠራሩን ተከትለው ድጋፍና ክትትል ሊያደረጉት እንደሚገባ ምክትል ሰብሳቢው አስገንዝበዋል፡፡
በአንዳንድ ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች በትምህርትና ጤና ተቋማት የደረጃ ዕድገትና የትርፍ ሰዓት ክፍያ መዘግየት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተት እየፈጠረ ስለመሆኑና ችግሩን ለመቅረፍ የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ በአፅንኦት እልባት እንዲሰጥ ያሳሰቡት ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ (ዶ/ር) ከህብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት የተጀመሩት የልማት ሥራዎች ዕቅድ ከግብ እንዲደርስ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመፍታት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ
የብልጽግና መንግስት ባለፉት አመታት የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማስጀመር ጠንካራ የሆነ ስራ እየሰራ ነው – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የዱራሜ ክላስተር የግብርና ሴክተር ባለሙያዎች “የመሐሉ ዘመን” በሚል ርዕስ ወቅታዊና ሀገራዊ ሰነድ ላይ ውይይት አካሄዱ