የአረካ ግብርና ምርምር ማዕከል ስድስት የተሻሉ የእንሰት ዝሪያዎችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

ሀዋሳ፡ የካቲት 28/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአረካ ግብርና ምርምር ማዕከል ስድስት የተሻሉ የእንሰት ዝሪያዎችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የአረካ ከተማ ዙሪያ አርሶ አደሮች ከማዕከሉ ያገኙት እንሰት በሽታን የሚቋቋምና በአጭር ጊዜ ምርት እንደሚሰጥ ተናገረዋል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ካሉት ሦስት የግብርና ምርምር ማዕከላት አንዱ የሆነው የአረካ ግብርና ምርምር ማዕከል የሀገራችን ግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በርካታ የምርምር ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

በዚህም ከ 611 በላይ የእንሰት ዝሪያዎችን በመሰብሰብ በቡልኣ፣ በቆጮና በቃጫ ምርት የተሻሉ ስድስት የእንሰት ዝሪያዎችን በመለየት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

አርሶ አደር አበበ አንጎሬ፣ ማዶዬ ማኖና ፍቅሬ ባልዳዳ በአረካ ግብርና ምርምር ማዕከል የተመረጡት የእንስት ዝረያዎችን በጓሯቸው በመትከል ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸው፥ ከእንሰት ዝሪያዎች መካከል ጋዋዳና ያምቡሎ የሚል መጠሪያ ያለውን እንሰት በድጋፍ መልክ ማግኘታቸውን የሚናገሩት አርሶ አደሮቹ፥ በቡልኣ፣ በቆጮና በቃጫ ምርት የተሻሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት የነበሩ ዝሪያዎች ስድስትና ሰባት ዓመታት ጠብቆ ለምግብነት እንደሚያውሉ ያስታወሱት አርሶ አደሮቹ፥ ከማዕከሉ አሁን የተገኙ አዲስ ዝረያዎች ግን በሁለት እና በሶስት አመታት ውስጥ ምርት ስለሚሰጡ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የእንሰት አጠውልግ በሽታ ለመከላከል በምርምር ማዕከሉ ከበሽታ ነፃ የሆኑትን በማብዛት ለአርሶ አደሮችና አብዥ ማህበራት እንደሚሰራጭ የሚናገሩት የብሔራዊ የእንሰት ምርምር አስተባባሪና የእንሰት ዝሪያ ማሻሻያ ተመራማሪ ሄኖክ ፍቅሬ ናቸው፡፡

በበሽታ የተጠቃውን እንሰት በመለየት ከማሳ በጥንቃቄ በመቆፈር እና በጥልቅ ጉድጓድ በመቅበር የበሽታውን ስርጭት መቆጣጠር እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

በምርምር ማዕከሉ የዘር ጥራት ቁጥጥር ተመራማሪና የመነሻ ቴክኖሎጂ ብዜት ሥራ ሂደት አስተባባሪ አስፋው ብረሃኑ፥ ከ611 በላይ የእንሰት ዝርያዎች ከምርምር ማዕከሉ የወጡ መሆኑን አመላክተው ከዚህ ውስጥ የተሻሉ ስድስት እንሰቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አምና ከመላው ሀገሪቱ 760 ሺ በላይ የእንስት ችግኝ ጥያቄ ቀርቦ 48 ሺ በላይ የእንሰት ችግኝ እንደተሰራጨ ተናግረዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በሦስት ሄክታር መሬት ለማባዛት እንዲሁም በአንድ ሄክታር መሬት ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን አቶ አስፋው ጠቁመዋል፡፡

የአረካ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ገነነ ገዛሃኝ በበኩላቸው ተቋሙ የእንስት ዝሪያ ምርምር እንደ ሀገር እየተመራ የሚገኝ መሆኑን አንስተው የእንሰት ችግኝ ፍላጎትና አቅረቦትን ለማመጣጠን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ድርሻዬ ጋሻው – ከዋካ ጣቢያችን