የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ ከእርግዝና ጊዜ ጀምሮ በአንድ ሺህ ቀናት ውስጥ የአመጋገብ ሥርዓትን በማሻሻል የባህሪ ለውጥ ለማምጣት ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ከተለያዩ ሴክተሮች ለተውጣጡ ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ጋር ተካሂዷል።
የስልጠናውን መድረክ በንግግር የከፈቱት የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምራት አሰፋ፤ ህፃናት እንዳይቀነጭሩ ከእርግዝና ጊዜ ጀምሮ እስከ አንድ ሺ ቀናት የተመጣጠነ ምግብ እንደሚያስፈልጋቸውና ይህን ለማድረግ በመንግስት ተቋማትና በማህበረሰቡ የተቀናጀ ስራና ርብርብ ማድረግ ይጠበቃል ብልዋል።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ታምራት አክለውም በዞኑ ካሉ 16 የመንግሥት ተቋማት የተውጣጡ የስርዓተ ምግብ ማሻሻል ቴክኒክ ኮምቴ አባላት በተቋማቸው የተመጣጠነ አመጋገብና በግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ የዕቅዳቸው አካል አድረገው እንዲመሩና ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ታሰቦ የተሰጠ ስልጠና መሆኑን አስረድተዋል።
እስከ 6 ወር ጡት ብቻ ማጥባትና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ለእናትም ለልጅም ጤና አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ የህፃናት መቀንጨርን ለመከላከል ጉልህ ሚና አለው ተብሏል።
በደቡብ ኦም ዞን ጤና መምሪያ የእናቶችና ህጻናት ጤና ማሻሻል ባለሙያ አቶ ሙሉቀን ከበደ፤ በጤናው ዘርፍ በዋናነት ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ የሚያደርገውን የተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓትና የምግብ ችግር ለመቅረፍ ከጤና ተቋማት በሻገር ሌሎችም መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በምግብ ዋስትናና በሥርዓተ ምግብ አቅደው እንዲሰሩ የሚያግዝ የጋራ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አቶ ታደለ ብርሃኔ እና ወ/ሮ እስከዳር አለማየሁ፤ የመንግሥት ተቋማት የተቋቋሙበት ዋነኛዉ አላማ በሁሉም ዘርፍ የህዝቡን ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በመሆኑ በሥርዓተ ምግብና በአመጋገብ ማሻሻል ላይ በጤና መምሪያ በኩል በቅንጅት ለመስራት የተጀመረው ተግባር አበረታች በመሆኑ ለውጤታማነቱ የጋራ ርብርብ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ስልጠናው ስራውን በእቅድ እንድንሰራና የህፃናት መቀንጨርን ለመታደግ የሚያስችል ነው ያሉት ተሳተፊዎቹ፤ በቀጣይ በሥርዓተ ምግብ ማሻሻል ላይ ከመምሪያው ጋራ በግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቱ መሰረት ዕቅዱን እስከታችኛው መዋቅር ድርስ አውረደው ለመስራት አቅጣጫ የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡ ጀታ ታገሰ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የጎፋ ዞን ደምባ ጎፋ ወረዳ ህዝብ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ተካሄደ
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ እንደ ሀገር ለተጀመረው ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ለውጥ የማይተካ ሚና እንዳለው ተገለፀ
ሠላምን በማፅናት ስራ የመንግስታት ግንኙነት እና ሃገረ መንግስት ግንባታ ወሰኝ መሆኑ ተገለጸ