ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ክልል አቀፍ የኪነ-ጥበብና ስነ-ጥበብ ውድድር ተጠናቀቀ

ሀዋሳ፡ የካቲት 28/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ላለፉት ሁለት ቀናት በታርጫ ከተማ ሲካሄድ የቆየው ክልል አቀፍ የኪነ-ጥበብና ስነ-ጥበብ ውድድር ተጠናቋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አዘጋጅነት በታርጫ ከተማ ሲካሄድ የነበረው ክልል አቀፍ የኪነ-ጥበብና ስነ-ጥበብ ውድድር በቤንች ሸኮ ዞን በሶስት ዘርፎች አሸናፊነት ተጠናቋል።

በማጠቃለያ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው መለዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፈ አቶ ፋንታሁን ብላቴ፥ በክልሉ ከፍተኛ የጥበብ አቅም ያላቸው በርካታ ወጣቶች መኖራቸውን ጠቁመው፥ የወጣቶቹን አቅም በማጎልበት ላይ ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የወጣቶቹን የኪነ ጥበብ አቅም በማቀናጀት በኪነ ጥበብ ዘርፍ የክልሉን ህዝብ አንድነትና ትስስር ከማጠናከር ባሻገር ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲጫወት መስራት ይገባል ብለዋል።

በውድድሩ የተሳተፉ ሁሉም ተወዳዳሪዎች የሚደነቅ የጥበብ ተሰጥኦ ማሳየት መቻላቸው ለሀገራዊ የኪነ-ጥበብና ስነ-ጥበብ ውድድር ብቁ የጥበብ ቤተሰብ ለማግኘት ረድቶናል ብለዋል ።

በሀገር ደረጃ ለሚደረገው የኪነ-ጥበብና ስነ-ጥበብ ውድድር የተመለመሉ አሸናፊዎች ከሙያተኞች ጋር በመሆን ከወዲሁ ልምምድ መጀመር እንዳለባቸውም የቢሮ ሃላፊ መልዕክት አስተላልፏል

ውድድሩን ከተሳተፉት መካከል አንዳንዶች በሰጡት አስተያየት የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፓርት ቢሮ በስነጥበብና ኪነጥበብ ያለንን ተስጥኦ እንድናወጣና አከባቢያችንን በጥበብ እንድናሳውቅ መድረኩን ላመቻቸው አካል ምስጋና እንደሚገባ ገልጸው፥ መሰል መድረኮች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በውድድሩ በሦስቱ ዘርፍ ማለትም በፎቶግራፍ፣ በስነ-ጹሑፍ፣ በሞዴሊንግ ቤንች ሸኮ ዞነ 1ኛ ሲሆን በስነ-ስዕል እና ፊልም ደግሞ ካፋ ዞን 1ኛ ሆኗል፤ በውዝዋዜ የዳውሮ ዞን አንደኛ ሲሆን ህፃን ቡዙፍሬ በዛብህ ልዩ ተሸላሚ ሆናለች፡፡

በመጨረሻም በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ላጠናቀቁት የምስክ ወረቀት የተሰጠ ሲሆን የተሳተፉትን የሁሉም ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፓርት መምሪያ ሃላፊዎችን፣ ውድድሩን የመሩትን ዳኞችንንና ሌሎችንም ታዳሚዎችን የቢሮ ሃላፊ አቶ ፋንታሁን አመስግነዋል ።

ዘጋቢ: አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን