ሀዋሳ፡ የካቲት 28/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአፈጣጠር ችግር ምክንያት በየአካባቢው ተደብቀው ያሉ ህጻናት ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው ሀገር አቀፍ የአፈጣጠር ችግር ሳምንትን “የላቀ ብሄራዊ የመከላከል ህክምና እና አካታች ስርዓት ለአፈጣጠር ችግሮች” በሚል መሪ ቃል በቡታጅራ ከተማ አክብሯል።
በየዓመቱ ከሚወለዱ ህጻናት ከሶስት እስከ ስድስት በመቶ የሚሆኑት ለአፈጣጠር ችግር የተጋለጡ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሀገር አቀፍ የአፈጣጠር ችግር ሳምንትን አስመልልቶ መልዕክት ያስተላለፉት የቢሮ ምክትል ኃላፊና የህክምና አገልግሎት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብቴ ገብረሚካኤል፥ የችግሩን አሳሳቢነት ለመቅረፍ እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይ በጤና ተቋማት ውስጥ የጤና አገልግሎት ጥራትን እና ፍትሃዊነትን መሠረት በማድረግ ለችግሩ የተጋለጡ ህፃናት ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአፈጣጠር ችግር ላለባቸው ዜጎች በቂ የሆነ የተሐድሶ ማዕከላት አለመኖር ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል የሚሉት አቶ ሀብቴ፥ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በቀጣይ እንደ ክልል ጠንካራ ስራዎች እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
በጤና ተቋማት ለእናቶችና ህጻናት የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን በተገቢው መልኩ እንዲያገኙ በማድረግና የአመጋገብ ስርዓትን በማሻሻል የአፈጣጠር ችግሮችን መከላከል እንደሚቻልም አስረድተዋል።
በዘርፉ በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖርና የህክምና ግብዓት እጥረቶች የሚጠቀሱ ችግሮች መሆናቸውን ያነሱት አቶ ሀብቴ ሆስፒታሎች ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል።
በየአካባቢው ለችግሩ የተጋለጡትን በማውጣት ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ የጋራ ጥረት ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል ።
በመድረኩ የተገኙት በኒያ ፋውንዴሽን የጆይ ኦቲዝም ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ኢሌኒ ዳምጠዉ እንዳሉት ማዕከሉ በአፈጣጠር ችግር ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ህጻናትን ለማገዝ መቋቋሙን ጠቁመው፥ አሁን ላይ በሃገር ደረጃ በሰባት ክልሎች በመንቀሳቀስ ለችግር የተጋለጡትን የመለየት፣ ግንዛቤ ማስጨበጥ እና ህክምና እንዲያገኙ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል ።
በመድረኩ የተሳተፉ አንዳንድ አካላት በበኩላቸው የትምህርት ዕድል ያላገኙ ህፃናት የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በትኩረት መስራት እንዳሚገባ ገልጸዋል ።
የኦቲዝም ተጠቂ ህፃናት ወላጆች በበኩላቸው የማዕከሉ መገንባት ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል ።
በዕለቱም በቡታጅራ በመቂቾ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የኦቲዝም ማዕከል ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነስርዓት የተካሄደ ሲሆን በትምህርት ቤቱ የሚገኘው ልዩ ድጋፍ የሚሹ ተማሪዎች ማዕከልም ተጎብኝቷል።
በመድረኩ የጤና ሚኒስትር እና የክልሉ ጤና ቢሮ የስራ ኃላፊዎች በክልሉ የሚገኙ ሆስፒታሎችና የጤና ሴክተር ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች አጋር አካላት ተሳታፊዎች ሆነዋል ።
ዘጋቢ፡ ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በካፋ ዞን ጨና ወረዳ በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FSRP) የተከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጋር የልምድ ልውውጥ ተደረገ
ሳታ ቴክኖሎጂ እና ቢዝነስ ኮሌጅ በአርባ ምንጭ ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያ ዲግሪ እና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስኮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 132 ተማሪዎችን አስመረቀ
በዕቅድ የሚመራ የመፈፀም አቅሙ ያደገ ሲቪል ሰርቫንት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን በደቡብ ኦሞ ዞን የሳላማጎ ወረዳ ሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤት ገለፀ