ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትምህርት ተሳትፎና ጥራት ላይ እየተስተዋለ ያለውን ክፍተት ለማረም የትምህርት አመራሩ በትኩረት መስራት እንዳለበት ተገለጸ

የቤንች ሸኮ ዞን አጠቃላይ የትምህርት አመራሮች የዞኑ የትምህርት ስራ አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት እያካሄዱ ነው።

በውይይቱ መድረክ ላይ የተገኙት የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ደግፌ ኩድን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትምህርት ተሳትፎና ጥራት ላይ እየታየ የመጣውን ክፍተት ማረም ይገባል ብለዋል።

የትምህርት ሥራ በርካታ ባለድርሻ አካላት ያሉት በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ በማስተባበርና በማቀናጀት የትምህርት አመራሩ በሚገባ መምራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ወርቁ እንደገለፁት፤ በትምህርት ተሳትፎ፣ ብክነትና በአጠቃላይ የትምህርት ስራ ላይ የሚታየውን የትምህርት ስብራት ለማረም ወሳኝ ወቅት ላይ ስለምንገኝ ርብርብ ይጠይቃል።

የመምሪያው ሀላፊ የሴክተሩን የእስካሁን እቅድ አፈፃፀም እና የመወያያ መነሻ ሀሳብ ሰነድ ለታዳሚያን ያቀረቡ ሲሆን ተሳታፊዎችም በተነሱት ጉዳዮች ላይ በመወያየት ላይ ይገኛሉ።

ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ – ከሚዛን ጣቢያችን