በከተማዋ የንፁ መጠጥ ዉሃ አቅርቦት እየተሻሻለ መምጣቱን የቦዲቲ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ

በከተማዋ የንፁ መጠጥ ዉሃ አቅርቦት እየተሻሻለ መምጣቱን የቦዲቲ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ

ሀዋሳ፡ የካቲት 28/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወላይታ ዞን የቦዲቲ ከተማ ነዋሪዎች በከተማው ያለው የንፁ መጠጥ ዉሃ አቅርቦት እየተሻሻለ መምጣቱ እንዳስደሰታቸው ገለጹ፡፡

ለከተማው ህብረተሰብ ንፁህ መጠጥ ዉሃ ለማዳረስ በሰፊዉ እየተሰራ መሆኑን የቦዲቲ ከተማ ዉሃና ፈሳሽ አገልግሎት ድርጅት አስታውቋል።

ወ/ሮ ዝናሽ ወልዴና አቶ በቀለ በርገነ የቦዲቲ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ፥ በአሁን ሰዓት የቦዲቲ ከተማ ነዋሪዎች የተሻለ የውሃ አቅርቦት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በከተማዋ ካለው ህዝብ ቁጥር ጋር የማይመጣጠን የውሃ አቅርቦት በመኖሩ ምክንያት በከፍተኛ የውሃ እጥረት ስንቸገር ነበር ያሉት ነዋሪዎቹ፥ አሁን ግን በከተማው ውሃን ለማዳረስ በተሰራው ሥራ ህዝቡ በቂ ዉሃ እያገኘ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ አስረድተዋል።

በከተማው በአንዳንድ ንግድ ሥራዎች ላይ ከዚህ በፊት በነበረው ውሃ እጥረት ምክንያት ይፈጠር የነበረው ችግር ተቀርፎ አሁን ላይ የተሻለ ውጤት መምጣቱን በከተማዋ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች አመልክተዋል።

አሁን ላይ በቦዲቲ ከተማ ያለው የውሃ አቅርቦት ለመጠጥነት ከማገልገል በተጨማሪ የከተማው ነዋሪ በከተማ ግብርና ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረጉን አቶ ጌቱ አበራ ገልጸዋል ።

ነዋሪዎቹ መንግስት በከተማው የሚሰራውን ንፁህ መጠጥ ዉሃ ሥራ አድንቀው በሚሰሩ የልማት ሥራዎች ሁሉ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

የከተማውን ዉሃ ከጉዳትና ከብክነት ለመጠበቅ ሞያዊ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑንም የቦዲቲ ከተማ ዉሃና ፈሳሽ አገልግሎት ድርጀት ባለሞያ አቶ እሸቱ በርገነ አስረድተዋል።

ለከተማው ማህበረሰብ ንፁህ መጠጥ ውሃ ለማዳረስ በውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር ከውሃ ልማት ፋንድ ብድር በተገኘ ድሃፍ ከ222 ሚለዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባ የዉሃ ፕሮጀክት አሁን ላይ ለከተማው ህዘብ ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የቦዲቲ ከተማ ዉሃና ፈሳሽ አገልግሎት ድርጅት ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ኤርምያስ አዲላ ተናግረዋል ።

በተጨማሪም በከተማዋ የ68 ኪ.ሎ ሜትር መስመር የውሃ ማሻሻያ እና ማስፋፊያ ሥራ ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ ኤርምያስ ጠቁመው፥ ለዉሃ ፕሮጀክት በብድር የተገኘው ገንዘብ ከህብረተሰቡ በታሪፍ ማሻሻያ ተሰብስቦ የሚከፈል መሆኑንም ኃላፊው አስገንዝበዋል።

የቦዲቲ ከተማ በፈጣን ዕድገት ላይ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ንፁህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦትን ለነዋሪዎች ተደራሽ ለማድረግ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የከተማው ከንቲባ አቶ ጳዉሎስ በቀለ ገልጸዋል።

የቦዲቲ ከተማ በውሃ ልማት ያሳየችውን ለዉጥ በሁለም ዘርፍ ለመድገም ሁሉም ሰዉ ባለበት ቦታ ጠንክሮ መስራት እንዳለበትም አቶ ጳዉሎስ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ ሰላሙ ማሴቦ – ከዋካ ጣቢያችን