በኢፌዲሪ ህዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤት አባላት የተመራው ቡድን በኮሬ ዞን እየተሠሩ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎበኘ
ቡድኑ፣ ከጉብኝቱ በተጨማሪ በዞኑ ሳርማሌ ወረዳ ዬሮ ቀበሌ ከማህበራዊ መሠረቶች ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በልማትና መልካም አስተዳደር ዙሪያ ዉይይት አድርጓል።
በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት እየሰጠ ያለውን የሳርማሌ ወረዳ አስተዳደር ህንጻ፣ መቅሬዲ – ሻሮ – ትፋቴ – የሮ – ሠገን የመንገድ ፕሮጀክት ላይ እየተሠሩ ያሉ የሻች መንቻ፣ ጉሙሬ ሐይጎ፣ ሶሮ ወንዝ፣ ሳርማሌ ቁጥር አንድ እና ጱሬ ወንዝ የመንገድ ድልድዮችን ቡድኑ ጎብኝቷል።
እየተገነቡ ካሉ ድልድዮች ሦስቱ የተጠናቀቁ ሲሆን በሁለቱ ወንዞች የድልድዩ ምሰሶዎች ስራ፣ ለሳርማሌ ቁጥር ሁለት ድልድይ ደግሞ የሳይት ርክክብ መደረጉ ተነግሯል።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የውሃ፣ የመስኖ፣ የቆላማ አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ(ዶ/ር)፣ የክልሉ ምክር ቤት አባላት፣ የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ፣ የዞኑ መንግስት ዋና ተጠሪ ጢሞቴዎስ በቀለ፣ የዞኑና ወረዳው አፈ ጉባኤዎች እና ሌሎች አመራሮችም በጉብኝቱ ተሳትፈዋል።
በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ከተለያዩ ማህበራዊ መሠረቶች ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በልማትና መልካም አስተዳደር ዙሪያ እየተወያዩ ያሉት የሕዝብ ተወካዮቹ፣ የኮሬ ዞን አስተዳዳሪን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሳርማሌ ወረዳ ከዬሮ ቀበሌም ከተለያዩ ማህበራዊ መሠረቶች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ ከአርባምንጭ በነጭሳር ብሔራዊ ፓርክ በኩል ዞኑን የሚያገናኝ መንገድ ያለመሠራት፣ የዬሮ ጤና ጣቢያ ተገንብቶ ያለመጠናቀቅ፣ የመድሃኒት አቅርቦት ችግር፣ የጸጥታ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ጥያቄዎችን ለሕዝብ ተወካዮቹ አቅርበዋል።
የሳርማሌ ቁጥር ሁለት ድልድይ እና የትምህርት ቤት ግንባታ መጓተት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር፣ ለመብራት ችግር ተስፋ የተጣለበት የሶላር ግንባታ ፈጥኖ ወደ ተግባር ያለመቀየር፣ የኔትወርክ እና ሌሎች ጥያቄዎችም እንዲመለሱ ነዋሪዎች አሳስበዋል።
የሳርማሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጎሹ ጌታቸው፤ የልማት ሥራዎች አቅም በፈቀደ መልኩ ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ እንደሆነ ገልጸው ወረዳው የሚችላቸውን ከሕዝቡና ባለድርሻዎች ጋር በመተባበር የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኮሬ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ በበኩላቸው፤ የራስን ህሊና ለሠላም ማዘጋጀትና ተያይዞ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸው ለሚነሱ የልማት እና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሁሉም ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የውሃ፣ የመስኖ፣ የቆላማ አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ(ዶ/ር)፤ በየደረጃው ያሉ እጥረቶችን ለመፍታት ጥረቶች መኖራቸውን እና ሀገሪቷና ዓለም እየተጓዘበት ያለበትን ሁኔታ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በአካባቢው መንግስት መፈታት የሚችሉትን ተባብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግና ሌሎቹ ደግሞ በየደረጃው ላሉ ባለድርሻ አካላት የሚደርሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በውይይቱ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ምላሽና ማብራሪያዎችን ሠጥተዋል።
ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/