ሂባ ፋዉንዴሽን ኢስላማዊ ድርጅት ከአንሷር የየቲሞችና አቅመ ደካሞች መርጃ ማህበር ጋር በመተባበር ለ40 አቅመ ደካሞች የረመዳን አስቤዛ ድጋፍ ማድረጉን ገለፀ

ሂባ ፋዉንዴሽን ኢስላማዊ ድርጅት ከአንሷር የየቲሞችና አቅመ ደካሞች መርጃ ማህበር ጋር በመተባበር ለ40 አቅመ ደካሞች የረመዳን አስቤዛ ድጋፍ ማድረጉን ገለፀ

የሂባ ፋዉንዴሽን ኢስላማዊ ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ ወጣት ሙባረክ አደም በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ ድርጅቱ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ የልማት ስራዎች በተለይም በንፁህ መጠጥ ዉሃ ቁፋሮ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

በተለያዩ ክልሎች 86 የሚሆኑ የንፁህ መጠጥ ዉሃ ጉድጓዶችን ማስቆፈሩን የገለፁት ስራ አስኪያጁ ይህን በጎ ተግባር በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

1ሺህ 446ኛዉ የረመዳን ፆምን ምክንያት በማድረግ ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘዉ ኢትዮ ፖልክዋኔ ሙስሊም ጀመዓ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በቀቤና ልዩ ወረዳ ከአንሷር የየቲሞችና አቅመ ደካሞች መርጃ ማህበር ጋር በመተባበር ለ40 ቤተሰቦች የአስቤዛ ድጋፍ ማድረጉን ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።

የአንሷር የቲሞችና አቅመ ደካሞች መርጃ ማህበር ምክትል ሰብሳቢ ወጣት ሰባዉዲን ከድር በበኩላቸዉ፤ ማህበሩ ከተመሰረተ ወዲህ አጋዥ አካላትንና ድርጅቶችን በማስተባበር አቅም ለሌላቸዉ ለአካባቢዉ ማህበረሰብ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበሩ በዘንድሮዉ የረመዳን ፆም ለ230 አቅመ ደካሞች የአስቤዛ ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የገለፁት ምክትል ሰብሳቢዉ፤ እስካሁን ለ85 ቤተሰቦች ድጋፍ ተደርጓል ነዉ ያሉት።

ማህበሩ እያደረገ ያለዉን በጎ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ጁሀር ጀማል እንዳሉት፤ አንሷር የቲሞችና አቅመ ደካሞች መርጃ ማህበር እያደረገ ለሚገኘዉ በጎ አድራጎት ተግባር ምስጋናቸዉን አቅርበዋል።

ማህበሩ እያደረገ ባለዉ ተግባር ጽ/ቤቱ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግም ሀላፊው ገልፀዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች በሰጡት አስተያየት በተደረገላቸዉ ድጋፍ መደሰታቸዉን ገልፀው ማህበሩ በየጊዜዉ አቅም የሌላቸዉን አካላት በመለየት ለሚያደርገዉ ድጋፍም አመስግነዋል።

ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን