ህዝቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑ ተገለፀ

ህዝቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑ ተገለፀ

የፌደራልና የክልል የህዝብ ተመራጮች ከጉራጌ ዞን አመራር አካላት ጋር በወልቂጤ ከተማ ተወያይተዋል።

የፌደራልና የክልል የህዝብ ተመራጮች በጉራጌ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች፣ ከተለያዩ ማህበራዊ መሠረት ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ሲደረግ መቆየቱ ይታወሳል።

ስለሆነም ተመራጮቹ በውይይት ወቅት በክፍተትና በጥንካሬ ባነሷቸው ጉዳዮች ላይ ከዞኑ ስራ አስፈፃሚዎች ጋር በወልቂጤ ከተማ የጋራ ውይይት ተደርጓል።

ተመራጮቹ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ መንግስት በራሱ እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አድንቀዋል።

ሆኖም በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ክፍተት በመኖሩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

የኤሌክትሪክ ተደራሽነት እና መቆራረጥ ማህበረሰቡን ከማማረር ባለፈ የእለት ተዕለት የስራ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ አንስተዋል።

እንደ ህዝብ ተመራጮቹ ገለፃ በዞኑ የጸጥታ ችግር ባሉባቸው አካባቢዎች በነዋሪዎች እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት ፈጥሯል።

የህብረተሰቡ ደህንነት ስጋት ለሆኑ አካባቢዎች ይበልጥ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም አንስተዋል።

ትምህርት ህዝባዊ መሰረት እንዲይዝ የተሰራው ተግባር የተሻለ መሆኑን በመግለፅ የተማሪዎችን ውጤት እና ስነምግባር ለማሻሻል የመምህራን ምደባና ጥራት ሊተኮርበት ይገባል ብለዋል።

የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ለመክፈት የተጀመረው ስራ ወደ ተጨባጭ ለውጥ መቀየር እንዳለበትም ተናግረዋል።

የቤንዚንና የናፍጣ አቅርቦት አጥረት ህብረተሰቡን ላልተገባ ወጪ የሚዳርግ በመሆኑ የአቅርቦት እጥረቱን ከመቅረፍ ጎን ለጎን አስፈላጊውን ቁጥጥር ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የኢንቨስትመንት መሬቶች ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ያሉት ተሳታፊዎቹ፤ ሳያለሙ ለአመታት አጥረው በሚያቆዩ ባለሀብቶች ላይ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ አበራ ወንድሙ፤ የተነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ መፈፀም የሚችሉትን በመለየት ይሰራል ብለዋል።

ተጀምረው በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጠው የነበሩ የውሃ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደተቻለ ሁሉ በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት ያቆሙና አዳዲስ ፕሮጀክቶች ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

አሁንም ችግሩን ለመቅረፍ ህብረተሰቡ፣ ባለሀብቶች እና አጋር ድርጅቶን በማስተባበር ይሰራል ብለዋል።

አቶ አበራ አክለውም የህብረተሰቡን የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ለማረም እንደሚሰራም አስረድተዋል።

የመድሀኒት አቅርቦት እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑንም በመግለፅ።

የአፈር ማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር አቅርቦት ጉድለት አለመኖሩን በማንሳት በመስኖ ፕሮጀክቶች የሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ኸይሩ መሀመድ በበኩላቸው፤ በዞኑ በሚገኙ መዋቅር ተመራጮች ከመራጩ ህዝብ ጋር ተወካዮች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በወረዳዎች ሲወያዩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ተጠይቀው ያልተመለሱ ጥያቄዎችና ምላሻቸውን በመለየት ክትትል እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ኸይሩ፤ የምክር ቤቱም ዓላማ በተወካዩ እምነት የሚያሳድር ማህበረሰብን መፍጠር መሆኑን አመላክተዋል።

ሕዝቡ በራሱ አቅም ላከናወናቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች እውቅና በመስጠት፤ ያልተሳኩትን ተመራጮቹ በየደረጃው ለአስፈፃሚው በማሳወቅ ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡ እንዳልካቸው ደሳለኝ – ከወልቂጤ ጣቢያችን