በጎፋ ዞን ፕላንና ልማት መምሪያ በ2017 በዞኑ በሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚገኙ የስነ ህዝብ ክበባት ዞናዊ የአሸናፊዎች አሸናፊ ጥያቄና መልስ ውድድር በሳውላ ከተማ ተካሄደ

በጎፋ ዞን ፕላንና ልማት መምሪያ በ2017 በዞኑ በሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚገኙ የስነ ህዝብ ክበባት ዞናዊ የአሸናፊዎች አሸናፊ ጥያቄና መልስ ውድድር በሳውላ ከተማ ተካሄደ

ሀዋሳ፡ የካቲት 26/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን ፕላንና ልማት መምሪያ በ2017 በዞኑ በሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚገኙ የስነ ህዝብ ክበባት ዞናዊ የአሸናፊዎች አሸናፊ ጥያቄና መልስ ውድድር በሳውላ ከተማ ተካሂዷል።

በዞናዊ የጥያቄና መልስ ውድድር ማስጀመሪያ ላይ የጎፋ ዞን ፕላንና ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ጉጃ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ያልተመጣጠነ የህዝብ ቁጥር ዕድገት በዞኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደር ለዕድገት የሚደረጉ ሩጫዎችን እየገታ መሆኑን አመላክተዋል።

እየተስተዋለ ያለውን ፈጣን የህዝብ ቁጥር እድገት በመቆጣጠር ከሀገር ኢኮኖሚ ጋር ማጣጣም እንደሚገባ አስረድተዋል።

የጥያቄና መልስ ውድድሩ በተማሪዎች መካከል የፉክክር ስሜት በመፍጠር በአካባቢ እንክብካቤና በስነ-ተዋልዶ ጤና ግንዛቤ በመፍጠር ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ውድድር መሆኑን አቶ ሙሉቀን አንስተዋል።

በመምሪያው የስነ-ህዝብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በኃይሉ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የስነ ህዝብ ጉዳይ በተገቢው መንገድ ከተመራ እድል፤ በአግባቡ ካልተመራ ደግሞ ፈተና በመሆኑ ለጉዳዩ ሁሉም አካል ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ውጤት ማምጣት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዞኑ የህዝብ ቁጥር ዕድገት ከኢኮኖሚው ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ በትምህርት፣ በጤናና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ተደራሽነትና ጥራት ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ገልፀው ችግሩን ለመፍታት የልማት ስራዎች በሚከናወኑበት ወቅት የስነ ህዝብ ጉዳይ ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤንነትን ለማሻሻል እና አነስተኛ ቤተሰብ ከኢኮኖሚ ጋር በተመጣጠነ መልኩ አካባቢ ጥበቃ ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት ትምህርት በመስጠት በልማት ፕሮግራሞች ውስጥ የወጣቶችን ተሳትፎ ከፍ ማድረግን ዓላማው ያደረገ ውድድር ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የህዝብ ቁጥር ዕድገት የነገውን ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የሚያደርግ በመሆኑ ህዝቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የተማሪዎችን ግንዛቤ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን የሳውላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አያለው ቦላዶ ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቶች የመልካም ትውልድ መፍጠሪያ ማዕከላት እንደመሆናቸው ትኩረት ሰጥተው በመሳተፍ ለሌሎች ግንዛቤ ሊፈጥሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የወጡት ተማሪ አንተነህ ጸጋዬ ከመሎ ኮዛ ወረዳ፣ ተማሪ አብነት ተሰማ ከቡልቂ ከተማ እንዲሁም ተማሪ አብሰላት ሙሉጌታ ከሳውላ ከተማ በሰጡት አሰተያየት፤ በውድድሩ የተሻለ የፉክክር መንፈስ መፈጠሩን አንስተው ውድድሩ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በቀላሉ ለመረዳት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በጥያቄና መልስ ውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ለወጡ ተማሪዎችና በስነ ህዝብ ክበብ የተሻለ ተግባር ለፈጸመው የሳውላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማበረታቻ ሽልማት ከመምሪያው ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን