በክልሉ ደን ጥበቃ በተሰሩ ስራዎች ውጤትን መሰረት ያደረገ የካርበን ክፍያን ማግኘት እንዲቻል የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ የካቲት 26/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ ደን ጥበቃ በተሰሩ ስራዎች ውጤትን መሰረት ያደረገ የካርበን ክፍያን ማግኘት እንዲቻል የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ “REDD ፕላስ ፕሮግራም” በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት ላይ ያተኮረ የስልጠና ፕሮግራሙ ተግባራዊ ከሚደረግባቸው 29 ወረዳዎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች በቦንጋ ከተማ ስልጠና መሰጠት ጀምሯል።
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለዉጥ ቁጥጥር ቢሮ ምክትልና የደን ጥበቃና ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ለማ ገብረሚካኤል እንደገለጹት፤ የ“REDD ፕላስ ፕሮግራም” በክልሉ ከጀመረ ወዲህ በደን ጥበቃና በኑሮ ማሻሻያ ዘርፍ ዉጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነዉ።
በተለይም በደን ጥበቃ በክልሉ 29 ወረዳዎች የተሰሩ ስራዎችን ዉጤት መሰረት በማድረግ የካርበን ክፍያ ወቅት እየደረሰ በመሆኑ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትን በተደራጀ መልኩ መረጃ ማጠናቀር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ፕሮግራሙ በደን ከለላ፣ በኑሮ ማሻሻያ፣ በአዳዲስ ችግኝ ተከላና መሰል መስኮች እያደረገ ያለዉ አስተዋጽኦ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።
ማህበረሰቡ የደን ጥበቃ ስራዎች ላይ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መቆየቱን ያነሱት አቶ ለማ፤ ባደረገው አስተዋጽኦ መጠን በካርበን ሽያጭ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት እንደሚገባም አሳስበዋል።
አሁን ላይ በእሳት እና በመሰል ምክንያቶች ደን ማውደም በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች እየታየ በመሆኑ የዚሁ ተጽዕኖ በአየር ንብረት ላይ ችግር እንዳያስከትል ከፍተኛ የሆነ ክትትል ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ሬድ ፕላስ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር የሪቾ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ በአየር ንብረት ቁጥጥር አባል ከሆነችበት ከ1992 ጀምሮ ከፍተኛ ለዉጥ እየተመዘገበ ነዉ ብለዋል።
በዚህ ረገድም በየጊዜው እየተቀረጹ በሚመጡ ፕሮግራሞች ለአየር ንብረት ለዉጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት እየተቻለ መምጣቱን አመላክተዋል።
በክልሉ በእስካሁኑ በአጠቃላይ 5 መቶ 86 ሺህ ሄክታር የደን ከለላ ማከናወን መቻሉንም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ አካባቢ ጥበቃና ኑሮ ማሻሻያ ላይ የሚሰራ በመሆኑ በዘርፉ የሚገኙ ባለሙያዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በመድረኩ የተለያዩ ጽንሰ ሀሳቦች ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎች በተለያዩ ባለሙያዎች እየተሰጠ ነዉ።
ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚሁ ስልጠና በክልል ደረጃ ፕሮግራሙ ተግባራዊ ከሚደረግባቸው 29 ወረዳዎች የተውጣጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነዉ።
ዘጋቢ፡ አሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/