በዞኑ የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ

የሸካ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2017 የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀምና ቀጣይ የስራ አቅጣጫ ላይ የምክክር መድረክ በማሻ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ የውይይት ሰነዶች ከመምሪያው በሚመለከታቸው አካላት የቀረበ ሲሆን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ላይ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን ለተሳታፊዎች ተገልጿል።

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የትምህርት ቤት ግንባታ፣ የመጽሐፍት ህትመት ተግባር፣ የመማሪያ መጽሐፍት ተደራሽነትን በየትምህርት መዋቅሩ ተደራሽ መደረጉና የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመምህራን መሰጠቱን ለውይይቱ ተሳታፊዎች ተገልጿል።

በቀጣይ የትምህርት ቤት አምባሳደሮችን የመለየት ተግባር፣ የምገባ መርሀ ግብር በልዩ ትኩረት ማከናወን፣ የትምህርት ቤቶችን ጥቅል ገቢ ኦዲት ማስደረግና ማረጋገጥ፣ የመምህራንን አቅም የማጎልበት ተግባር፣ የተማሪዎችን የመማሪያ መጽሐፍት የማዳረስ ስራ መስራትና ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

በዞኑ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋትና የትምህርት ስብራትን ለመጠገን አንድ የአዳሪ ትምህርት ቤት መክፈት አስፈላጊ በመሆኑ ይህን ከዳር ለማድረስ በትኩረት እንደሚሰራም ነው የተገለጸው።

ከዚህ በተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን የማሻሻል ተግባር እንደሚሰራና የመምህራን ጥቅማጥቅም የማስከበር ተግባር እንደሚከናወን በሰነድ አቅራቢዎች ተጠቁሟል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ትምህርት ቤቶች ላይ ወርሀዊ ሪፖርት ያለመኖር እና ኦዲት ያለማድረግ ክፍተቶችን በመቅረፍ እንዲሁም የመማሪያ መጽሐፍት ተደራሽ ማድረግ ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠይቀዋል።

አሁን በመማር ማስተማር ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ በዞኑ የአዳሪ ትምህርት የማስጀመር ተግባር መልካም መሆኑን በመግለፅ ትኩረት በመስጠት ሊሰራ እንደሚገባም ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

የሸካ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን አለሙ በበኩላቸው፤ በአንድራቻ ወረዳ ጎጃ ትምህርት ቤት የተጀመረው የምገባ ስርዓት በሌሎች ትምህርት ቤቶች አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ፤ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጉዳዮች ሀሳብ አስተያየት የሰጡ ሲሆን ትምህርት ቤቶችን ከሌሎች ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ ጋር በማቀናጀት ለመማር ማስተማር ምቹ ሁኔታ መፍጠር ላይ አሁንም በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍት እጥረት ለውጤት መቀነስ አንዱ መንስኤ ስለሚሆን ከወዲሁ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ነው ብለዋል።

በዞኑ አዳሪ ትምህርት ቤት ለማስጀመር የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አመራር ቦርድ፣ የማናጅመንት አባላትና ሁሉም ባለድርሻ አካላት እያደረጉ ያለው ድጋፍ የሚመሰገን መሆኑን ገልፀው ለተግባራዊነቱ ዞኑ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ፣ የዞን፣ የከተማና የወረዳ እንዲሁም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ ምንታምር አስፋው – ከማሻ ጣቢያችን