ሀዋሳ፡ የካቲት 26/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩት ሴቶች እየቆጠቡ ውጤታማ እንዲሆኑ የድጋፍና ክትትል ሥራ እየተሠራ መሆኑን የቡርጂ ዞን የሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ዩኒት አስታወቀ።
በዞኑ የተደራጁ ሴቶች ገቢያቸውን በማሻሻል ከዚህ በላይ ውጤታማ ለመሆን ጠንክረው እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የቡርጂ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ዩኒት ኃላፊ ወ/ሮ ማርያም አየለ፥ ሴቶች በተለያዩ የልማት ቡድኖች ላይ ተደራጅተው በመቆጠብ ሠርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የድጋፍና ክትትል ሥራ በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በአትክልት እና ፍራፍሬ፣ በሰብል ምርት፣ ዶሮ እርባታ፣ አነስተኛ ንግድ እና በመሳሰሉት የሥራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ውጤታማ የልማት ቡድኖች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በግል “የወ/ሮ ሀጌ ሳሌ የዶሮ እርባታ” እና በልማት ቡድን ደግሞ “ብርሃን የሴቶች አትክልት እና ሰብል አምራች” ውጤታማ እየሆኑ ካሉት ለአብነት ያነሱት ኃላፊዋ በአሁኑ ስዓት ሠርተው ካገኙት ገቢ ቆጥበው ሥራቸውን በማሳደግ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ወ/ሮ ሀጌ ሳሌ የመንግስት ሠራተኛ ሲሆኑ ከሚያገኙት ደሞዝ በተጨማሪ የእንቁላል ዶሮ እና የአንድ ቀን ጫጩት ሥራ በ50 ሺህ ብር ጀምረው፥ እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን እያረቡ እንቁላሎችን እና የአንድ ቀን ጫጬቶችን አሳድገው ለገበያ እያቀረቡ በመሸጥ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከሁለት መቶ እስከ 3 መቶ ሺህ ብር ድረስ ተጨማሪ ገቢ አንደሚያገኙ አስረድተዋል።
ወ/ሮ ሀጌ ካላቸው ልምድ ሌሎች ሁለት ሴቶችን ከራሳቸው ጋር አደራጅተው የአንድ ቀን ጫጩት በብዛት አስገብተው በመሥራት የኢኮኖሚ አቅም ለማሻሻል ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
ብርሃን አትክልት እና የሰብል አምራች የልማት ቡድን ወ/ሮ አየለች ግንቤ እና የሺ ጩቴ በ14 አባላት ሆነው በመደራጀት ያመረቱትን ለገበያ በማቅርብ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ገልጸዋል።
በመኸር እርሻ ካመረቱት ጤፍ 16 ኩንታል ምርት ያገኙትን ሽጠው 72 ሺህ ብር ባንክ መቆጠባቸውን የሚናገሩት እናቶቹ ከአትክልት ቲማትም፣ ጥቅል ጎመን፣ ቃሪያ፣ ካሮት እና ድንች እያለሙ በመሸጥ ይበልጥ ምርታማ ለመሆን ጠንክሮ እየሠሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡ አብዶ አያላ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በካፋ ዞን ጨና ወረዳ በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FSRP) የተከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጋር የልምድ ልውውጥ ተደረገ
ሳታ ቴክኖሎጂ እና ቢዝነስ ኮሌጅ በአርባ ምንጭ ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያ ዲግሪ እና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስኮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 132 ተማሪዎችን አስመረቀ
በዕቅድ የሚመራ የመፈፀም አቅሙ ያደገ ሲቪል ሰርቫንት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን በደቡብ ኦሞ ዞን የሳላማጎ ወረዳ ሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤት ገለፀ