ሀዋሳ፡ የካቲት 26/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የፌደራልና የክልል የህዝብ ተመራጮች በኮሬ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች፣ ከተለያዩ ማህበራዊ መሠረት ከተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እያደረጉ ነው።
በውይይቱ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የሀገር ሽማግሌ አቦ ወንድማገኝ ሳዲሳ፣ አቶ ተማሙ ጀማል፣ ደሳለኝ ደርጋሱ እና ሌሎችም ከዘጠኝ ዓመታት በላይ በዘለቀው የጸጥታ ችግር የሞት፣ የንብረት ውድመት፣ የመንገድ መዘጋት ችግሮች፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ማስከተላቸውን ጠቁመው፥ በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ብናነሳም ዘላቂ መፍትሔ አልተገኘለትም የሚሉት የከተማዋ ነዋሪዎቹ፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ያልተፈታ መሆኑን አመላክተዋል።
ከዲላ ወደ ኮሬ ዞን የሚወስደው መንገድ መዘጋቱ፣ ከጀሎ እና ዶርባዴ ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ያለመመለሳቸው፣ የንብረት ውድመትን ጨምሮ ሌሎች ችግሮችም በመኖራቸው እስካሁን ዋጋ እያስከፈለን ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ መንግስት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በፌዴራል መንግስት ተጀምሮ የተቋረጠው የፍስሃ ገነት – ኬሌ – ነደሌ መንገድ፣ የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጦ ግንባታው ያልተጀመረው በኬሌ ከተማ የማጻ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ የኔትወርክ መቆራረጥ እና የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮች ከተለያዩ ማህበራዊ መሠረቶች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል አጽንኦት ሰጥተዋል።
ተሳታፊዎቹ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ክትትልና ድጋፍ እንደሚያስፈልጉና የልማት ፍትሃዊነት እንዲኖር የጠየቁ ሲሆን በትምህርትና ጤና ዘርፍም ትኩረት እንዲደረግ አሳስበዋል።
የኮሬ ዞን የሽግግር ምክር ቤት ዋና አፌጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ አካላት በቀለ፣ ህገመንግስቱ በሰጠው ዕድል ከመራጩ ህዝብ ጋር ተወካዮች ከተለያዩ የህብረተሰብ ከፍሎች ጋር እየተወያዩ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት የተጠየቁ ጥያቄዎችና ምላሻቸውን የመለየት ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት አፈጉባኤዋ፥ የምክር ቤቱም ዓላማ ሞጋች ማህበረሰብን መፍጠር መሆኑን አመላክተዋል።
የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የውሃ፣ የመስኖ፣ የቆላማ አከባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር)፣ ከዚህ በፊት ህዝቡ የጠየቋቸው ጥያቄዎች አንዳንዶቹ እየተመለሱ እንደሆኑና ሌሎች ደግሞ በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ ከሁሉ በላይ የጸጥታው ጉዳይ መሰረታዊ መሆኑን አብራርተዋል።
አንዳንድ ችግሮች ከሀገራዊ ሁኔታ ጋር የሚያያዙ ናቸው የሚሉት ዶክተር አወቀ፥ በተገኙ አጋጣሚዎች ያልተመለሱ ጥያቄዎች የሚፈቱበት መንገድን መፈለግ እንደሚገባ ጠቁመው፥ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲሰጡ ይደረጋል ነው ያሉት።
ሕዝቡ በራሱ አቅም ከአካባቢው ባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት የሚችላቸውን አብሮ በመሥራት መፍታት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል
ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/