በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በ6 ወራት የግብርና ሥራዎች አፈፃፀምና በቀሪ የበልግ ወቅት ንቅናቄ ተግባራት ዙሪያ ውይይት ተደረገ

በዞኑ የበልግ የእርሻ ወቅት በሁሉም የሰብል አይነቶች 78 ሺህ 200 ሄክታር መሬት በማልማት ከ4 ሚሊዮን በላይ ኩንታል የሠብል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

ባሳለፍነው 2016 የምርት ወቅት፤ የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት በመጠቀም በአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ሰብሎች 73 ሺህ 700 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ4 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት የተገኘበት ዓመት እንደነበር የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደግፌ ተናግረዋል።

ከእርሻ መካናይዜሽን፣ የመደበኛ መስኖና ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አኳያ የተሻለ ውጤት የታየበት የግብርናው መሥክ መሆኑን አንስተዋል።

ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚያሸጋግሩን የሰብል ምርቶች አኳያ የታየው ውስንነት ግን በቀጣይ ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በየምርት አመቱ የሚመረተው ምርት ከሚታረሰው ማሳ ጋር ሲነፃፀር ውስን መሆኑን ገልጸው፤ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሻሻል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በግብርናው ዘርፍ የአርሶአደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መንገድ ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ሊመራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአዝዕትና ሆርቲካልቸር፣ የቡና ልማትና ግብይት ሥራዎች፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ አረንጓዴ አሻራና የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ የግብዓት አቅርቦትና ማህበራትን ለማጠናከር በተከናወኑና በታቀዱ ጉዳዮች ዙሪያ ገለፃ ቀርቧል።

በዞኑ የበልግ የእርሻ ወቅት በሁሉም የሰብል አይነቶች 78 ሺህ 200 ሄክታር መሬት በማልማት ከ4 ሚሊዮን በላይ ኩንታል የሠብል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ዘርፍ ኃላፊው አቶ ዮሐንስ በየነ ባቀረቡት ሰነድ ገልጸዋል።

በዞኑ አብዛኛው በልግ አብቃይ አካባቢዎች አስፈላጊው የእርሻ ዝግጅት መደረጉን ከየመዋቅሩ የተሳተፉ አመራሮች ተናግረዋል።

ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሻገር የሚያስችሉ የሰብል ምርቶችን በወቅቱ የማሳ ልየታ አድርጎ ከመሥራት አኳያ ቀጣይ ሰፊ ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

ከግብዓት ዋጋ ንረት ረገድም ከአርሶአደሩ የሚነሱ ቅሬታዎችን በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች መተማመን ላይ መደረሱንም አስተያየት ሰጪዎቹ አንስተዋል።

የጎፋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደለ ያዕቆብ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲ አደረጃጀቶች ዕቅድን ለይተው ወደ ተግባር እንዲገቡ በማድረግ ተረጂነትን በምርታማነት ማሸነፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አጸደ አይዛ፤ በክልሉ ሀገራዊ ኢንሼቲቮች አኳያ ያለው አፈጻጸም ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን አንስተው አጠቃላይ የግብርናውን እንቅስቃሴ ከመደገፍ ረገድ ልዩ ትኩረት ይሻል ብለዋል።

ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን