ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ ከተለመደው የመንግስት የስራ ሰዓት ውጭ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ ከተለመደው የመንግስት የስራ ሰዓት ውጭ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ የካቲት 24/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቀጣይ ወራት ቀሪ ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ ከተለመደው የመንግስት የስራ ሰዓት ውጭ መስራት እንደሚያስፈልግ በኮሬ ዞን የኬሌ ከተማ አስተዳደር ገለጸ።

“ቃልን ወደ ባህል ጸጋን ወደ ገቢ” በሚል መሪ ቃል የቀሪ ወራት የንግድ እና ገቢ ማሰባሰብ ንቅናቄ መድረክ በኮሬ ዞን ኬሌ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የኬሌ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮርዳኖስ ጭርዶ፣ ለከተማ ዕድገት ገቢን መሰብሰብ መሠረት መሆኑን ጠቁመው፥ ባለፉት ሰባት ወራት 41 ሚሊየን 214 ሺህ ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ 36 ሚሊየን 131 ሺህ ብር በላይ ማሳካታቸውን ገልጸዋል።

ከመደበኛ ገቢ አንጻር የVAT እና TOT ደረሰኞችን የመስጠትና ጠይቆ የመውሰድ ችግሮች በመኖራቸው ሊቀረፍ በሚችልበት መንገድ መሥራት እና ውዝፍ ዕዳዎችን ለይቶ ማስመለሱ ላይ በቀጣይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

አምራችና ሸማቹን በማገናኘት ገበያን ለማረጋጋት ተጀምሮ የተቀዛቀዘው የሰንበት ገበያን ማጠናከር የቀሪ ወራት ትኩረት መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

የኬሌ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ዮሐንስ ኃይሉ በበኩላቸው፣ በመሪ ቃሉ መነሻ በሚቀጥሉ ወራት ሰፊ ተግባር የሚጠብቀን በመሆኑ በመንግስት የሥራ ሰዓት ብቻ ሰርተን ውጤታማ ልንሆን አንችልም ብለው፣ ባለጉዳዮች ወደተቋማት እንዲመጡ በማበረታታት በየትኛውም ጊዜ ተጨማሪ ሰዓት በመጠቀም መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ካልሰራን ከሕዝብ ጋር ለልማት የተግባባነውን ማሳካት አንችልም የሚሉት ከንቲባው፣ ሁሉም በሰዓትም ሆነ ከሰዓት ውጭ ለመሥራት ዝግጁ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

ያሉንን ጸጋ በአግባቡ ከተጠቀምን ገቢን ማሰባሰብ እንችላለን፤ አሁን ላይ ከተማዋ ካስመዘገበችው የፈርጅ ለውጥ አንጻር ተያይዞ የሚመጡ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ማትኮር አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

በመድረኩ ከዞኑም ሆነ ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ናቸው።

ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን