እንደ ዓድዋ ሁሉ በአንድነትና በመደመር መንፈስ በጋራ ቆመን ድህነትን ድል ማድረግ ይገባል – አቶ ደስታ ሌዳሞ
እንደ ዓድዋ ጀግኖች አርበኞች ልዩነቶቻችንን ትተን በአንድነትና በመደመር መንፈስ በጋራ ቆመን ድህነትን ድል ማድረግ ይገባናል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
የአድዋ ድል 129ኛ ዓመት በዓል በሲዳማ ክልል ደረጃ በሀዋሳ ከተማ ዛሬ ተከብሯል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ቀኑን ስናከብር እንደተለመደው መዘከር ብቻ ሳይሆን ለድል ያበቁን ጥበቦች ምንድን ናቸው የሚለውን መፈተሽ ይገባናል ብለዋል።
ጀግኖች አርበኞች ዛሬ ያለችውን ሀገር ያስረከቡን ከጠላት ጋር ተመጣጣኝ አቅም ኖሯቸው ሳይሆን በሀገር ፍቅርና በነበራቸው ህብር ማሸነፍ በመቻላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
የሀገር ፍቅር ሲኖር ህይወትን ለመስጠት ወደ ኋላ አይባልም ያሉት አቶ ደስታ፤ አባቶቻችንም ውድ ህይወታቸውን ሰውተው የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ተምሳሌት የሆነውን ድል አስገኝተውልን ዛሬ በኩራት እንድንኖር አስችለውናል ነው ያሉት።
የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ በበኩላቸው፤ አድዋ የኢትዮጵያውያንና የመላው ጥቁር ህዝቦች የጋራ ትግል ውጤት ነው ብለዋል።
ይህን ድል እኛም እንደ ጀግኖች አርበኞች አባቶቻቸችን በወርቅ ብዕር ለመጻፍ እንድንችል በጋራ በመቆም በሉዓላዊነታችን ላይ በሚቃጡ ማንኛውም ጉዳይ ላይ ራሳችንን መስጠት አለብን ነው ያሉት።
በበዓሉ ላይ ከተሳተፉት መካከል የስካውት አባል የሆነው ወጣት እያደር ውብሸት እንዳለው፤ ወጣቱ ያለውን አቅም ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን ማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በማዋል ለሀገሩ እንደ ዓድዋ ጀግኖች መስዋዕትነት ሊከፍል ይገባል።
ጀግኖች አባቶቻችን፤ በታጠቀው ዘመናዊ መሳሪያና በሰለጠነ ሰራዊት ታግዞ የመጣውን ቅኝ ገዢ ድል እንዳደረጉት ሁሉ እኛም አሁን ጠላታችን ድህነት ላይ ዘምተን የበለጸገች ሀገር ለተተኪዎቻችን እናወርሳልን ማለቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ስካውት ኬራት እንግዳወርቅ በበኩሏ፤ ጀግኖች አባቶቻችን ለሀገር በከፈሉት መስዋዕትነት ዛሬ እኛ በኩራት ለመኖር በቅተናል ነው ያለችው።
እኛም እንደ ጀግኖች አባቶቻችን የስካውት አባል ስንሆን በዘር፣ በቀለም በሀይማኖትና በሌሎች ጉዳዮች ሳንለያይ አንድ ሆነን ለማገልገል ቃል በመግባት ነው ብላለች።
ይህን ቃል በማክበርም እንደ ጀግኖች አርበኞቻችን እኛ ወጣቶች ብዙ ልንሳተፍባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ በዋናነት ድህነትን ማሸነፍ በመሆኑ ድህነትን ታግለን ለመጣል በተሰማራንበት መስክ የሚጠበቅብንን እንወጣለን ነው ያለችው።
በበዓሉ ላይ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራልና የሲዳማ ክልል ፖሊስ ሰራዊት አባላት፣ ጀግኖች አርበኞች፣ ስካውቶች፣ ተማሪዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተወካዮች ተገኝተዋል።
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/