“ህያው ድል”

ህያው የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ድል በዓል …ዓድዋ…ዋ…ዋ…

በትውልድ ቅብብሎሹ ዛሬ እስካለንበት ድረስ የማይነጥፍ ህያው ድል የሆነው የዓድዋ ድል በየዓመቱ የካቲት 23 ድሉን በመዘከር የሚከበር ሲሆን ዘንድሮ ለ129 ጊዜ በድምቀት ይከበራል፡፡ ይህ ታላቅ ድል ኢትዮጵያን በዓለም እንድትነግስ ያደረገ ትልቅ የድል ብስራት ነው፡፡

ጣሊያን ኢትዮጵያን ቅኝ እገዛለሁ በሚል ያሰበችውን ህልሟን አክሽፈው ጀግኖች አያቶቻችንም የሰውን ክብርና የነፃነቱን ልዕልና በዓለም ከፍ አድርገው ለመላው ጥቁር ህዝብ የተስፋ ብርሀን የሆኑበት ድል ነው – የአድዋ ድል፡፡

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክሩለታል።

ሌሎች የአውሮፓ ወራሪ ኃይሎች እንዳደረጉት ሁሉ የጣሊያን ወራሪ ኃይልም ኢትዮጵያን ቅኝ ሊገዛ ባሕር አቋርጦ፣ ድንበር ጥሶ መጣ። ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በወቅቱ ጠላትን ድል ነሡ!

እዚህ ላይ ታዲያ የሰለጠነ ዘመናዊ ጦር ሳይገነቡ፣ የሀገራቸውን ፍቅር ታጥቀው የዘመቱትን ኢትዮጵያውያን በመምራት፣ ደማቅ ታሪክ ጽፈዋል፡፡

ንጉስ ምኒሊክም ከኢትዮጵያ ንጉስነታቸው አልፎ ዓለም ያወቃቸውና ያከበራቸው ሆነው ህያው ድልን ዛሬ ድረስ እያከበርን ቀጣይም በኩራት የምናስረከበውን የታሪክ ህያው አሻራቸውን ትተውልን አልፈዋል፡፡ ታዲያ ለዚህም ህያው ድል ትውልዱ የተሰማውንና በተረዳው ልክ ስለ ዓድዋ ህያው ድል ታሪካችን በዜማቸው ተቀኝተውለታል፡፡

“የሰው ልጅ ክቡር ሰው መሆን ክቡር፤

ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን ሰውን ሲያከብር፤

በደግነት በፍቅር በክብር ተጠርቶ፤

በክብር ይሄዳል ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ፤”……

በማለት “ጂጂ” ስለ ሰው ክቡርነት ስለ ዓድዋ ድል በሚገባ ስትቃኝ፤ በተመሳሳይ “ቴዲ አፍሮ” “ጥቁር ሰው” በሚል የሙዚቃ ስራው ንጉሱን ከፍ አድርጎ ያወደሰው፤ ስለንግቲቷም እጤጌ ጣይቱ ″የኛ የሙዚቃ ባንድ‶ “ጣይቱ እመቤቲቱ” በማለት አዚመውላታል፡፡ እነዚህና ሌሎችም ህያው ለሆነው የዓድዋ ድል ትውልዱ ተቀኝቶለታል፡፡

ከግንባር ቀደሙ የፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኞች አንዱ ነው – ትውልደ ጃማይካዊው ማርከስ(ማርቆስ) ጋርቬይ። ይህ ስመ ጥር ፖለቲከኛ አድዋን እንዲህ ይገልጸዋል። “የአድዋ ድል ማለት ጥቁሮች ትልቅ ስኬት ለማስመዝገብ ብቁ እንደሆኑ ብሎም ዝቅ ተደርገው መቆጠር እንደሌለባቸው ለዓለም ያረጋገጠ ድል ነው”፡፡ ጀግኖች አባቶች እና እናቶች ቅኝ ያልተገዛች ሀገርን ለአሁኑ ትውልድ ያስረከቡት አብሮነታቸውን በማጠናከርና በጀግንነት ነው።

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የአለም ጥቁር ህዝቦች እኩልነትና ነጻነት ትግል መጎልበት ትልቁን ሚና ተጫውቷል።

ልክ የዛሬ 129 ዓመት በዓድዋ ተራሮች ዓለም በተለይም አውሮፓውያን ያልጠበቁት ክስተት ተፈጠረ። አውሮፓውያን እንደቅርጫ የተከፋፈሉት ጥቁር ሕዝብ ድል አደረጋቸው።

ይህ ወሳኝ ድል የሀገራችንን ቀጣይነት ያለው ነፃነት ያረጋገጠ ሲሆን ኢትዮጵያ የአውሮፓ ቅኝ አገዛዝን በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የቻለች ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር እንድትሆን አድርጓታል።

ይህ ስኬት የተመዘገበው ደግሞ በላቀ የጦር ስትራቴጂ፣ በኢትዮጵያ ኃይሎች መካከል በነበረው አንድነት እና ኢትዮጵያውያን ስለ ነፃነት አስፈላጊነት በነበራቸው ግንዛቤ ምክንያት እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።

በየዓመቱ በመላው ኢትዮጵያ የካቲት 23ን ትውልዱ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት የሚያከብሩት ታላቅ የጥቁሮች የነፃነት ህያው የድል በዓል ነው፡፡

ህያው የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ድል በዓል ….ዓድዋ…ዋ…ዋ…

አዘጋጅ ፡ ብዙነሽ ዘውዱ