የጡረታ ገንዘብ ክፍያ በአቅራቢያቸው ያለመፈፀሙ ለተጨማሪ ወጪና እንግልት እያጋለጣቸው መሆኑን በዳውሮ ዞን ከጪ ወረዳ የሚገኙ ጡረተኞች ገለፁ

ችግሩን ለመፍታት  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑን  በመንግስት ሠራተኞች ጡረታና ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የዳውሮ ዞን ጽ/ቤት አስታውቋል

ቅሬታቸውን ለደሬቴድ ዋካ ኤፍ ኤም የገለፁት የጡረታ አበል ተከፋዮች በሀገር መከላከያ ሰራዊት እና በተለያዩ የመንግስት መ/ቤቶች በመንግስት ሠራተኛነት  በተለያዩ አካባቢዎች እና ተቋማት ለህዝብና መንግስት በማገልገል ለጡረታ  የበቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ለጡረታ ከወጡ ጊዜ ጀምሮ ተከፋይ አበላቸውን በቅርብ ርቀት በሚገኘው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቢሆንም አሁን ላይ ወደ ዳሸን ባንክ በመዛወሩና  የባንኩ ቅርንጫፍ በአቅራቢያቸው ባለመኖሩ ከከጪ የቶጫ ወረዳን አቋርጠው እስከ ማሪ  በመሄድ ለከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ እና እንግልት እየተጋለጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

እነዚህም ከወረዳ ጫፍ አካባቢ እስከ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት በእንግልት ተጉዘው ጡረታቸውን ለማግኘት እንደሚገደዱ አስረድተዋል።

የሚከፈላቸው የጡረታ ገንዘብ በመጠን የተለያየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አንዳንዶች የሚያገኙት ክፊያ  በእግር ካልተጓዙ በስተቀር የትራንስፖርት ወጪ ከሚያገኙት ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ  አለመሄድን እየመረጡ እንደሆነ ገልፀው ችግሩ እንዲፈታ ከወረዳ ጀምረው የሚመለከታቸውን አካላት በተለያዩ አግባቦች እየጠየቁ ቢሆንም እስካሁን ግን መፍትሔ አለማግኘታቸውን ነው የሚገልጹት።

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የከጪ ወረዳ ዋና    አስተዳዳሪ አቶ ውለታው ሁሴን ጡረታ የሚከፍለው የዳሽን ባንክ ቅርንጫፍ በወረዳም ይሁን በቅርብ አካባቢ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ የተከሰተ  ችግር መሆኑን ጠቅሰው ይኸንንም ጡረተኞች በተደጋጋም ለወረዳው አስተዳደር ቅሬታ እያቀረቡ መቆየታቸውን አንስተዋል። 

የወረዳው የጡረተኞችን የርቀት ጉዞ ፣ አላስፈላጊ ውጪ እና እንግልትን ለማስቀረት የሚያደረገውን ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ  ለሚመለከተው አካል የማሳወቁን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አቶ ውለታው አስታውቀዋል።

በመንግስት ሠራተኞት ጡረታ ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የዳውሮ ዞን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደስታ መንገሻ በዞኑ 4000 የሚደርሱ ጡረተኞች እንዳሉ በመጠቆም እነዚህም በተገባው ውል መሰረት በዳሽን ባንክ የጡረታ ክፍያ እንደሚያገኙ፤ ጡረተኞች በእርጅና ወቅታቸው የጡረታ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ መጉላላት ስለማይገባቸው በየወሩ በቅርበት ክፍያቸው እንዲፈፀም እያደረጉ ያሉትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

ዘጋቢ፦ ዮሐንስ መካሻ ከዋካ ጣቢያችን