ኮሚቴ አባላቱ በሳውላ ማረሚያ ተቋም ከወላጆቻቸው ጋር የሚገኙ ህፃናትንና ወጣት ጥፋተኞችን አያያዝ ጉብኝት አደረጉ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ የሚመሩ የክልሉ ህጻናት መብቶች ኮንቬንሽን ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በሳውላ ማረሚያ ተቋም ከወላጆቻቸው ጋር የሚገኙ ህፃናትንና ወጣት ጥፋተኞችን አያያዝ ጉብኝት አድርገዋል።
ቢሮው በተቋሙ ለሚገኙ ህፃናት፣ ተማሪዎች እና ለሴቶች የአልባሳት፣ የንፅህና መጠበቂያና ልዩ ልዩ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍም አድርጓል።
ሳውላ ማረሚያ ተቋም ኃላፊ ኢ/ር ብርቱኳን መንግስቱ ለኮሚቴው አባላት ባደረጉት ገለጻ በተቋሙ የሴት ታራሚዎች፣ ህፃናትና ወጣት ጥፋተኞች ያሉበትን አጠቃላይ ሁኔታ አብራርተዋል።
ኃላፊዋ በትምህርት አሰጣጡ ሂደት ላይ የማጣቀሻ መጻህፍት ዕጥረት መኖሩን ለኮሚቴው ገልጸው፤ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት አኳያ የነበረውን ችግር በመፍታት በተደረገው ሰፊ ጥረት በ2 ወር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ወደ ስራ ይገባል ብለዋል።
በግቢው ለሁሉም ታራሚዎች የህክምና አገልግሎት የሚሰጥበት ተቋም ቢኖርም ከመድሀኒት አቅርቦት አኳያ ክፍተት መኖሩንም ተናግረዋል።
አልፎ አልፎ ግብረሰናይ ድርጅቶች የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርጉ የተናገሩት ኃላፊዋ፤ ነገር ግን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሴት ታራሚዎች ማደሪያዎች፣ ከእናቶቻቸው ጋር በማረሚያ ተቋሙ የሚገኙ ጨቅላ ህፃናት ያሉበት ሁኔታ፣ የወጣት ታራሚዎች የትምህርት አሰጣጥ ሂደት፣ የመመገቢያና መጸዳጃ እንዲሁም የተደራጁ ሴቶች የሥራ እንቅስቃሴ በኮሚቴው አባላት ተጎብኝተዋል።
በተቋሙ ለሚገኙ ህፃናት፣ ለተማሪዎች እና ለሴቶች የአልባሳት፣ የንፅህና መጠበቂያና ለግማሽ ሴሚስተር የሚሆኑ ልዩ ልዩ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍም ተደርጓል።
ጉብኝቱን አስመልክተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊና የአብይ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ካሰች ኤልያስ በሰጡት አስተያየት፤ በማረሚያ ተቋሙ የሚስተዋሉ የሴቶች ሰብአዊ መብት አያያዝ ያለ ጥፋታቸው በማረሚያ ተቋሙ የሚገኙ ህፃናት መብትና ደህንነት የወጣት ጥፋተኞች ማቆያ ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለይቶ በጋራ ለመፍታት ያለመ ጉብኝት መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በተናጠል ችግሮችን ለይቶ ለኮንቬንሽኑ ኮሚቴ አባላት ይቀርብ እንደነበር ያነሱት ወ/ሮ ካሰች፤ ነገር ግን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ችግሩን በሥፍራው ተገኝተው እንዲመለከቱትና መሥተካከል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ የየበኩላቸውን ድርሻ እንዲወስዱ ለማስቻል የሚረዳ ነው ብለዋል።
ከዚህም ውስጥ የህጻናት ማቆያ ያለበት ደረጃና ሴቶችን በተለያዩ መሥኮች አደራጅቶ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ የተሠራው ሥራ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
ነፍሰጡር ታራሚዎች በውጪ የህክምና ተቋማት የጤና ክትትል እንዲያደርጉ መደረጉና በግቢው ህክምና ተቋማት የሚስተዋለው የመድሃኒት እጥረት በኮሚቴው ባለድርሻዎች በፍጥነት እልባት ማግኘት እንደሚገባው አሳስበዋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊና ህፃናት ዘርፍ ኃላፊ የኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ምህረት በላይ በበኩላቸው፤ በተቋሙ የሚገኙ ህፃናት መብትና ደህንነትን በማስበቅ ሂደት የንጽህና፣ ህክምናና ሌሎችንም መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው መሟላታቸውን መከታተልና ጉድለቶችንም ፈጥነው እንዲታረሙ ከማድረግ ረገድ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ወጣት ጥፋተኞች የራሳቸው ማቆያ ሊኖረው ይገባል ያሉት ወ/ሮ ምህረት ነገር ግን በተቋሙ ከትላልቅ ወንድ ታራሚዎች ጋር ተቀላቅለው በአንድ ቤት መኖራቸው ቀጣይ መታረም የሚገባው መሆኑን አፅኖት ሠጥተዋል።
በማረሚያ ተቋሙ የሚገኙ ህፃናት አስፈላጊውን ቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲያገኙ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል ወ/ሮ ምህረት።
የህግ ታራሚ ሴቶች በሰጡት አስተያየት፤ ለልጆቻቸው በማረሚያ ተቋሙ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸው ለቢሮውና ባለድርሻ አካላት ምሥጋና አቅርበዋል።
የጉብኝቱ ተሳታፊ የክልሉ ህጻናት መብቶች ኮንቬንሽን ቴክኒክ ኮሚቴዎች ከክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ ማረሚያ ተቋም፣ ፍትህ ቢሮ፣ ጤና ቢሮ እና ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተውጣጡ አባላት ናቸው።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ ከክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር ከክልሉ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ ሴቶች ስልጠና መስጠት ጀመረ
ምክር ቤቱ ታች ድረስ በመውረድ የክትትልና ቁጥጥር ስራ በመስራቱ የውሸት ሪፖርት መጠን በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን የሲዳማ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ገለፀ
በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የህዝቡን የልማት ፍላጎት በሚመጥን መልኩ ምላሽ ለመስጠት አመራሩ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለበት የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት አሳሰበ