የይዞታ ማረጋገጫ ምዝገባ በማከናወን የደን ባለቤትነትን በመፍጠር የህብረተሰቡን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ የካቲት 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የይዞታ ማረጋገጫ ምዝገባ በማከናወን የደን ባለቤትነትን በመፍጠር የህብረተሰቡን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትየጵያ ክልል የደን፣ አከባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው በዲላ ከተማ በክልሉ ለሚገኙት ነባር ደኖች የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ምዝገባ ማስጀመሪያ ንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
የክልሉ ደን፣ አከባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቴ ግጄ የደን ባለቤትነትን በመፍጠር የህብረተሰቡን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ደንን ማልማት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ቢሮው ከገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የደን መሬቶች የባለቤትነት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ምዝገባ በማስጀመር ከምዝገባው የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በክልሉ ሰው ሠራሽ፣ የማህበረሰብ፣ የግለሰብ፣ የእምነት ተቋማትና ባህላዊ ደኖችን በመለየት የባለቤትነት ማረጋገጫ እንዲኖረው በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን አቶ ግዛቴ አስረድተዋል።
የተጎሳቆለ መሬት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ፣ በመጠበቅና በመንከባከብ ለሀገራችን ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና የሥነ- ምህዳር ጥቅም እንዲውል የፋይናንስ አቅም እንዲኖር ለማድረግ በጸደቀው የልዩ ፈንድ አዋጅ ላይ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር ለተግባራዊነቱ በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል፡፡
በንቅናቄው መድረክ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) መንግሥት በግብርና ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ ካለው አረንጓዴ አሻራ አንዱ መሆኑን ጠቁመው፥ አሁን ካለው 23 ነጥብ 3 በመቶ የደን ሽፋን በ2030 ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አሰረድተዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ከችግኝ ዝግጅት ጀምሮ በቅንጅት በመከወን ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ መሠራት እንዳለበት አስተባባሪው አስገንዝበዋል፡፡
ደኖችን ማልማት ብቻ ግብ አለመሆኑን የገለጹት ዶ/ር መሪሁን፥ የተተከሉና በይዞታ ማረጋገጫ ምዝገባ የተለዩ ደኖችን ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲጠብቅ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመድረኩ የመግባቢያና የተጎሳቆሉ መሬቶች ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ለማቋቋምና አስተዳደሩን ለመወሰን የወጣ አዋጅ ዙሪያ ሰነዶች እየቀረቡ ሲሆን በክልሉ ከሚገኙ ከ12ቱ ዞኖች የተወጣጡ ባለድርሻዎችና የቢሮው ማናጅመንት አባላት ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያ
More Stories
ከ2.5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ለዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የአንድ ማዕከል አገልግሎት ድጋፍ ማድረጉን የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ገለጸ
የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት መደበኛ ጉበኤ በዲመካ ከተማ ማካሄድ ጀመረ
የገቢ ግብር የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎትን ከመመለስ ባለፈ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ ለመሆኑ ተገለጸ