ከ2.5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ለዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የአንድ ማዕከል አገልግሎት ድጋፍ ማድረጉን የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ገለጸ

ከ2.5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ለዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የአንድ ማዕከል አገልግሎት ድጋፍ ማድረጉን የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ገለጸ

ሀዋሳ፡ የካቲት 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከ2.5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ለዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የአንድ ማዕከል አገልግሎት ድጋፍ ማድረጉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ገልጿል::

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ የኢንተርፕራይዞች ቆጠራ፣ ምዝገባና ዋና ዋና ተግባራት ግምገማ በወልቂጤ ከተማ መካሄድ ጀምሯል::

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ እንደገለፁት፤ የስራ ዕድል የሚፈጠርላቸው ኢንተርፕራይዞችና ወጣቶች መረጃን በአግባቡ ለመሰነድና ዲጂታላይዝ ለማድረግ እንዲያግዝ በማለም ለዞኖችና ለልዩ ወረዳዎች ለአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚውል የኮምፒውተር ድጋፍ ተደርጓል::

በዚህም ባለው ውስን በጀት በመጠቀም ከ2.5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተገዙ የቴክኖሎጂ ቁሶች መሆናቸውን የገለፁት ሀላፊው፤ ለታለመለት አላማ ብቻ መገልገል እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል::

ድጋፍ የተደረገላቸው ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በበኩላቸው፤ ለዜጎች ዘላቂ የስራ ዕድል ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት አጋዥ የሆነና ዘመኑን የሚመጥን ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልፀዋል::

በግምገማ ሂደቱ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የአፈፃፀም ሪፖርት አቅርበው ጠንካራ ጎኖችና የተስተዋሉ ጉድለቶች ላይ ውይይት በማድረግ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ይመላከታል ተብሎ ይጠበቃል::

ዘጋቢ፡ መሀመድ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን