የገቢ ግብር የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎትን ከመመለስ ባለፈ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ ለመሆኑ ተገለጸ

የገቢ ግብር የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎትን ከመመለስ ባለፈ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ ለመሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ የካቲት 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የገቢ ግብር የህብረተሰቡንና የመንግስትን የልማት ፍላጎትን ከመመለስ ባለፈ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ በመሆኑ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ የሸኮ ከተማ ግብር ከፋዮች ተናገሩ።

በሸኮ ከተማ አስተዳደር ካነጋገርናቸው ግብር ከፋዮች መካከል አቶ አዲሱ ምትኬ፣ አቶ ጴጥሮስ ሽፈራውና አቶ ካሳሁን ገዳ በሰጡት አስተያየት ግብር የዜግነት ግዴታ በመሆኑ በወር ከ4 እስከ 7 ሺህ ብር በላይ እንዲሁም በዓመት ከ60 እስከ 80 ሺህ ብር በላይ ግብር እየከፈሉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ግብርን በወቅቱና በአግባቡ መክፈል የመንግስትና የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት የሚመልስ ከመሆኑም ባለፈ የተከፈለ ገንዘብ በተጨባጭ ልማት ላይ እየዋለ መሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎች ገልፀዋል።

ግብርን ከከፈልን ትርፍና ኪሳራችንን ለይተን እናውቃለን ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ የንግድ ፈቃድ አውጥተው መስራት ከጀምሩበት ጊዜ አንስቶ የገቢ ተቋም በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶቹን በመስጠትና በባለሙያ በመታገዛቸው የተሻለ አፈፃፀም እንዳላቸው ተናገረዋል።

በከተማ አስተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት 48 ሚሊየን በባለፉት 6 ወራት ደግሞ ከ25 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰበሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱም ተገልጿል።

በዚህም በመደበኛና በማዘጋጃ ቤታዊ አገለግሎት፣ በቀጥታና ቀጥታ ያልሆነ ታክስ እንዲሁም ታክስ ያልሆነ የገቢ ርዕሶች በባለፉት 6 ወራት 25 ሚሊየን 499ሺህ 796 ብር ገቢ ለመሰበሰብ ታቅዶ 34 ሚሊየን 83 ሺህ 298 ብር ከዕቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ንጉሴ ዱዳብ ተናገረዋል።

ለዕቅዱ መሳካት የገቢ ተቋሙ ቁርጠኝነት፣ ታክስ ላይ የዴስክ ኦዲት ማደረግ፣ የባለድርሻ አካላት የትምህርት፣ የጤና፣ የትራንስፖርት፣ ከፖሊስ ተቋማትና የፊት አመራሮች ጋር በቅንጅት በመሰራቱ እንደሆነ አስተባባሪው ገልፀዋል።

የገቢ አሰባሰብን አጠናክሮ በማስቀጠል ረገድ ዘርፉን ለማሻሻል ትምህርትና ስልጠና እንደሚያስፈልግ ያወሱት አቶ ንጉሴ በተለይም ከባለሙያ ዕጥረት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።

በተቋሙ የባለድርሻ አካላት ወጥ ያለመሆን፣ ከቡና አቅራቢዎችና የመሳሰሉት ድርጅቶች የቫትና ቲኦቲ ደረሰኝ በመሰበሰብ ቁጥጥርና ክትትል አናሳ የመሆን ዕጥረቶች በሩብ ዓመቱ የተስተዋሉ ችግሮች በመሆኑ በቀጣይ እንዲፈታ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ንጉሴ አሰረድተዋል።

ሳይፈቀዱ የተያዙ መሬቶችና የፕላን ተቃርኖ ያላቸው ህገ ወጥ ቤቶችን በተመለከተ የክልል መስተዳደር ምክር ቤት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተሠረቶ ግብር እንዲከፈልባቸው ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።

ከአዳዲስ ነጋዴዎች ጋር ተያይዞ የአሻራና የሲስተም አለመስራት ችግሮች በአገለግሎት አሰጣጥ ላይ ጫና እያሳደረ በመሆኑ ይህን ለመፍታት ከዞኑ ገቢዎች መምሪያ ጋር በቅንጅት ለመስራት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስተባባሪው ገልጿል፡፡

የጣሪያና የግድግዳ ግብር ከሐምሌ1 እስከ ታህሳስ 30 የክፍያ ወቅት ቢሆንም ከመደበኛ ግብር ውጭ አደርጎ የማየት ችግሮች እንደነበረ አቶ ንጉሴ ገልፀው ከተማውን የሚመጥን ግብርን በመሰበሰብና የታክስ ህግን በማስከበር ረገድ የሁሉም ሚና እንደሚጠይቅ አስገንዘበዋል።

ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን