የህዝቡን የልማት ተሳትፎ በማጠናከር የከተማውን ዕድገት ለማፋጠን በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቦኖሻ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ
ሀዋሳ፡ የካቲት 17/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የህዝቡን የልማት ተሳትፎ በማጠናከር የከተማውን ዕድገት ለማፋጠን በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን በሀድያ ዞን የቦኖሻ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡
የቦኖሻ ከተማ መስራች በነበሩት በልጅ ግዛው ደምሴ መታሰቢያነት በከተማው የሚገነባው ታሪካዊ ሀውልት የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የቦኖሻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ባሀሩ ነመና ለእንግዶቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በከተማው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ቁጥርና የልማት ፍላጎት ለማመጣጠን በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
የጤና፣ የትምህርት፣ የንፁህ መጠጥ ዉሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የመንገድና መሰል መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት እንዲቻል የችግሮቹን ደረጃ በመለየትና ቅደም ተከተሉን በማስያዝ ልዩ እቅድ ተዘጋጅቶለት ወደ ስራ መገባቱንም ከንቲባው አብራርተዋል።
የዚሁ የከተማ ልማት አካል የሆነውና የከተማው መስራች በነበሩት በአቶ ግዛው ደምሴ መታሰቢያነት የሚገነባው ታሪካዊ ሀውልት በልጆቻቸው ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ መቀመጡንም አቶ ባሀሩ ገልጸዋል።
ለዚህም መላውን የከተማውን ነዋሪዎች፣ ተወላጆች፣ አጎራባች ወረዳዎችና ዞኖችን ሌሎች የልማት አጋሮችንም በማነቃነቅ የልማቱ ተሳታፊ በማድረግ ወደ ተግባር መገባቱንም ጠቁመዋል።
በወቅቱ ተገኝተው የመሰረት ድንጋዩን ያኖሩት የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪና ተወካይ አቶ ታምራት አኑሎ በበኩላቸው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ገድል የፈጸሙ የጦር ጀግኖች፣ የሳይንስ ጠበብቶች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና የተለያዩ ገድሎችን የፈጸሙ ጀግኖች ያሉባት አገር ናት ብለዋል።
ከእነዚህም መካከል ሀገርን ከመበተን ያዳኑ እንደነ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ እና በአድዋ ላይ ጀብድ የፈፀሙ እንደነ ፊታውራሪ ጌጃ ጋርቦ ዓይነት ጀግኖችን ያፈራች ምድር ናት ሀድያ ያሉት አቶ ታምራት፤ የቦኖሻ ከተማ መስራች ለነበሩት ለልጅ ግዛው ደምሴ መታሰቢያነት በከተማው የሚቀመጠው ሀውልት በልጆቻቸው እና በህዝብ ተሳትፎ እንዲገነባ ከተማ አስተዳደሩ ያደረገው አስተዋጽኦ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የቦኖሻ ከተማ መስራች የነበሩት የአቶ ግዛው ደምሴ ልጅ አቶ ዳንኤል ግዛው መላውን ቤተሰብ በመወከል ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከተማን ለኑሮ ምቹና ማራኪ ለማድረግና ለማሳደግ የሐውልት ግንባታውን ጨምሮ የከተማውን ደረጃ ከፍ በሚያደርጉ ዘርፎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል::
ያነጋገርናቸው አንዳንድ የከተማ ነዋሪዎችም በቦኖሻ ከተማ አስተዳደር የተጀመሩ በርካታ የልማት ስራዎች በህብረተሰቡ ተሳትፎና በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ባለበት ወቅት ለአቶ ግዛው ደምሴ መልካም ተግባር መታሰቢያ የሚሆን ታሪካዊ ሀውልት በልጆቻቸው ወጪ ሊገነባ የመሠረት ድንጋይ መቀመጡ ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
በከተማው የልማት እንቅስቃሴ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
ዘጋቢ: በየነ ሰላሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
”እንዳይረሳ ቅድሚያ ለደኅንነት” በሚል መሪ ቃል የትራንስፖርትና መንገድ ዘርፍ የሕዝብ ንቅናቄ መድረክ ተካሄደ
ሚዲያው ለህብረተሰቡ የመረጃ ምንጭ ከመሆን ባለፈ የሚታዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ በትኩረት መስራት እንዳለበት ተጠቆመ
በወላይታ ዞን አረካ ከተማ ሱማሞ አካባቢ የሚገነባውን አየር ማረፊያ ግንባታን የሚያስጀምር ልዑክ አረካ ከተማ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት