ሚዲያው ለህብረተሰቡ የመረጃ ምንጭ ከመሆን ባለፈ የሚታዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ በትኩረት መስራት እንዳለበት ተጠቆመ
የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሚዛን ቅርንጫፍ ጣቢያ የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ ላይ የሚዛን ቅርንጫፍ ጣቢያ የልማት ዕቅድ ባለሙያ አቶ መካሻው ከበደ ባለፉት 6 ወራት በጣቢያው የተሰሩ ስራዎችን ዕቅድ አፈፃፀም በዝርዝር አቅርበዋል።
በዚህም ባለፉት 6 ወራት በጣቢያው በተለያዩ የስርጭት ቋንቋዎች 5 ሺህ 210 የሬዲዮ ዜናዎች፣ 922 የሬዲዮ ፕሮግራሞች ተዘጋጅተው ለአየር መብቃታቸውን ገልጸዋል።
በቴሌቪዥን ኬዝ 131 የቴሌቪዥን ዜናዎችና 20 የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።
የውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ ሬዲዮ ጣቢያው የህዝቡ የመረጃ ምንጭና ተደማጭነት ያለው ጣቢያ ለመሆን የሚያስችሉ የተለያዩ ይዘቶችን በመቅረጽ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ይሁን እንጂ ጣቢያው ይበልጥ ተደማጭ እንዳይሆን በዞኑ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ተደራሽ ያለመሆን፣ የማሰራጫ ቁሳቁሶች እጥረትና ብልሽት እንዲሁም የሰራተኞች ጥቅማጥቅም በወቅቱ አለመድረስ የመሳሰሉ ችግሮች እያጋጠመው እንዳለ አንስተዋል፡፡
የቅርንጫፉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ትዕዛዙ ኬንጫ እንደተናገሩት፤ ባለፉት 6 ወራት በጣቢያው የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል።
በተለይ ጣቢያው ወቅታዊ ጉዳዮችን ትኩረት በማድረግ ሳቢና ተደማጭነት ያለው ሚዲያ ለመፍጠር ቢጋር ከማሻሻል ጀምሮ የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ በረከት ኢዮብ በበኩላቸው፤ ተቋሙን በስራዎቹ ማስተዋወቅ፣ የማርኬቲንግ ስራዎች ማስፋትና ከተቋማት ጋር መልካም ግንኙነትን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ እንደገለፁት፤ በሬዲዮ ጣቢያው ያለው የሰው ሀይል መነቃቃትና የስራ ሞራል ጥሩ የሚባል ነው፡፡
በተለይም ሚዲያው ለህብረተሰቡ የመረጃ ምንጭ ከመሆን ባለፈ የሚታዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ በትኩረት መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የሚዛን ቅርንጫፍ መልካም እና በርካታ ተግባራት በጠንካራ ጎን የሚጠቀሱ አፈጻጸሞች እንዳሉ ጠቁመው ጥራት፣ ፍጥነትና የሚዲያ አማራጮች ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን የስራ ሃላፊዎች የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
የህዝቡን የልማት ተሳትፎ በማጠናከር የከተማውን ዕድገት ለማፋጠን በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቦኖሻ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ
”እንዳይረሳ ቅድሚያ ለደኅንነት” በሚል መሪ ቃል የትራንስፖርትና መንገድ ዘርፍ የሕዝብ ንቅናቄ መድረክ ተካሄደ
በወላይታ ዞን አረካ ከተማ ሱማሞ አካባቢ የሚገነባውን አየር ማረፊያ ግንባታን የሚያስጀምር ልዑክ አረካ ከተማ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት