ውጤታማ የሆነ ስራ የሰራ አካባቢ ተጨማሪ ፕሮጀክት የማግኘት ዕድል አለው – ሚ/ር ዴኤታ የትምጌታ አስራት

ውጤታማ የሆነ ስራ የሰራ አካባቢ ተጨማሪ ፕሮጀክት የማግኘት ዕድል አለው – ሚ/ር ዴኤታ የትምጌታ አስራት

ሀዋሳ፣ የካቲት 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ውጤታማ የሆነ ስራ የሰራ አካባቢ ተጨማሪ ፕሮጀክት የማግኘት ዕድል እንዳለው የኢፌዴሪ ከተማና መሠረተ ልማት   ሚኒስትር  ዴኤታ የትምጌታ አስራት ተናገሩ፡፡

የኢፌዴሪ ከተማና መሠረተ ልማት   ሚኒስቴር  በወልቂጤ ከተማ  አስተዳደር የተሰሩ ስራዎችን እየተመለከተ ይገኛል።

ከተማ አስተዳደሩ በተለይ ባለፉት ስድስት ወራት የተሰሩ የመሠረተ ልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያዎችን አቅርቧል።

4 ነጥብ 5 ሄክታር  ቤት መስሪያ እና 2 መቶ ሄክታር መሬት ለኢንደስትሪ ልማት ስራ መካለሉን የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ ሙራድ ከድር አብራርተዋል።

አገልግሎት የማዘመን ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ነው ከንቲባው ያነሱት

25 ኪሜ የኮሪደር ልማት ስራ ለማከናወን ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።

ለዚህም ወሰን ከማስከበር ጀምሮ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ሙራድ አብራርተዋል።

የከተማው ነዋሪ 19 ሚሊየን ብር በከተማው ለሚሰሩ የመሠረተ ልማት ግንባታ እስካሁን እንዳዋጣ ተገልጿል ።

በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የመሰረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ የትምጌታ አስራት በወልቂጤ  ከተማ የህብረተሰቡን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የተሠራው ስራ የሚበረታታ ነው ብለዋል። የአከባቢውን የገቢ መጠን ማሳደግ መቻል እንዳለበት ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተሰሩ ስራዎች ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል  ነው ያሉት

በተያያዘ ዜና በወልቂጤ ማዕከል የሚገኘው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ  ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ በህብረተሰብ ተሳትፎ 109ኪሜ መንገድ መገንባት መቻሉን ምክትል ቢሮ ሃላፊው አማን ኑረዲን ገልፀዋል። 

በአዲስ መንገድ ግንባታ በነባር ጥገናና በድልድይ ግንባታው ቢሮው ያጠናቀቃቸው እና በመገንባት ያሉ ፕሮጀክቶች መኖራቸው ተጠቁሟል። ተቋሙ የተሽከርካሪ እጥረት ስላጋጠመው በሚጠበቀው ልክ ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉ ተነስቷል።

በመንገድ ስራው የተሟላ መረጃ መያዝ ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የትምጌታ አስራት ክልሉ ሰፊ ዕቅድ ከመያዙ አንፃር የሰራቸው ስራዎች ቢኖሩም የቀሩ ስራዎችን በፍጥነት ማጠናቀቅ ይገባል ብለዋል።

ያልተለቀቀ በጀትን በተመለከተ ውጤት ከታየ በኋላ የሚለቀቅ በመሆኑ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ አለበት ተብሏል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተሽከርካሪን የመሳሰሉ ድጋፎችን በተመለከተ አቅሙ የቻለውን ያደርጋል ተብሏል።

ዘጋቢ:ሲሳይ ደበበ