በሐዋሳ ከተማ ህዝባዊ ኮንፍራንስ እየተካሄደ ነው።
ሀዋሳ፣ የካቲት 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የብልጽግና ፓርቲ ”ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል በ 2ተኛ መደበኛ ጉባኤ ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር ከተማ አቀፍ ህዝባዊ ኮንፍራንስ በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ውይይቱን የሚመሩት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌ እና የቱሪዝም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ ናቸው።
የብልጽግና ፓርቲ በምስራቅ አፍሪካ በርካታ አባል ያለው ግዙፍ ፓርቲ ነው ያሉት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌ ከ 15 ሚሊየን በላይ አባላት አለው ብለዋል።
ፓርቲው ከፋፋይ ትርክቶችን በመተው ህብረብሔራዊ አንድነት ላይ አተኩሮ እየሰራ ያለ እውነተኛ ፓርቲ ስለመሆኑ ጠቁመው በተለይ የትላንት ቁርሾዎችንና ዕዳዎችን በመተው ምንዳዎችን ይዞ የቀጠለ ፓርቲ ነው ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ለህዝቡ ቃል በገባው መሠረት ለቃሉ የታመነ እውነተኛ የህዝብ ፓርቲ ነው ያሉት ዶክተር ካሳሁን ኢትዮጵያ ከስንዴ ተመጽዋችነት ወደ ስንዴ ላኪነት ያሻገረ ፣ የማይቻሉ የሚመስሉ ህልሞች እውን ያደረገ ቃልንም ባህል ያደረገ ፓርቲ ነው ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ከተመሠረተ የ 5 ዓመታት አጭር ዕድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም በነዚህ ጥቂት አመታት አማላይ ስኬቶችን እያስመዘገበ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በውይይቱ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ ባለፉት 7 ወራት በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ሪፖርት አቅርበዋል።
በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ምዕራፍ የተከፋፈለ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
2ተኛው ምዕራፍ ከ 4 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ተመድቦ ከተማዋን ለማስዋብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የውስጥ ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ እየሰራ ነው ያሉት ከንቲባ መኩሪያ መርሻዬ እስካሁን የተሰበሰበው ገቢ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 596 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው ብለዋል።
ዘጋቢ :- አብደላ በድሩ
More Stories
ከመግፋፋት በመውጣት የመደመር ዕሳቤን በማጎልበት በህዝቦች መካከል ያሉ ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ
የዲላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስክ ያስተማራቸውን 518 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
ውጤታማ የሆነ ስራ የሰራ አካባቢ ተጨማሪ ፕሮጀክት የማግኘት ዕድል አለው – ሚ/ር ዴኤታ የትምጌታ አስራት