የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ

የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ

‎“የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ቃል የ2017 ዓ.ም የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓል በአርባምንጭ ከተማ ተከብሯል፡፡

‎የዕለቱ የክብር እንግዳ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እመቤት ወንድሙ፤ በሀገራችን አካል ጉዳተኞች የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

‎ህብረተሰቡም ማግለልና መድሎ በማቆም፣ አካል ጉዳተኝነት አለመቻል እንዳልሆነ በመገንዘብ ከጎናቸው እንዲሆንና ሁሉም ተቋማት የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ የዕቅዳቸው አካል አድርገው እንዲሰሩ ጭምር አሳስበዋል፡፡

‎የክልሉ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ደነቀ ዳሾ፤ የበዓሉ ዓላማ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ስለ አካል ጉዳተኞች እና አካል ጉዳተኝነት በማስገንዘብ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዋኖ ዋሎሌ፤ በዓሉ ሲከበር ቀደም ሲል የተሰሩ ስኬቶችን በማንሳትና በቀጣዩ ደግሞ ውጤታማ ስራ በመስራት ነው ብለዋል፡፡

‎ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮም አካል ጉዳተኞችን በሁሉም ረገድ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የ10 ዓመት ዕቅድ በማዘጋጀት ግብ ጥሎ እየሰራ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

‎በአካል ጉዳተኞች ላይ ያሉ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን በመቅረፍ እኩል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በቅንጅት ልንሰራ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

‎ተሳታፊዎችም እንዲህ አይነት መድረኮች ለአካል ጉዳተኞች ወሳኝና መስራት እንደሚችሉ የሚያሳይና ህብረተሰቡም ግንዛቤ የሚያገኝበት በመሆኑ ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡

‎ዘጋቢ፡ ብርሃኑ ዳሾ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን