በተቀናጀ በተፋሰስ ልማት ሥራ የታዩ ለውጦችን ለማስቀጠል አርሶአደሮች በንቃት መሳተፍ እንደሚገባቸው በጌዴኦ ዞን የዲላ ዙሪያ ወረዳ አስታወቀ።

በተቀናጀ በተፋሰስ ልማት ሥራ የታዩ ለውጦችን ለማስቀጠል አርሶአደሮች በንቃት መሳተፍ እንደሚገባቸው በጌዴኦ ዞን የዲላ ዙሪያ ወረዳ አስታወቀ።

ሀዋሳ፣ የካቲት 14/2017 ዓ/ም (ደሬቴድ) በወረዳው በ2017 ዓ/ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ፣ ያረጀ ቡና ጉንደላና ነቀላ፣ ለአዳዲስ ተከላ የጉድጓድ ዝግጅት፣ የመንገድ ጠረጋና የድልድይ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በወረዳው በጎላ ቀበሌ ህብረተሰቡ በመንገድ ሥራ እያከናወነ አግኝተን ካነጋገረናቸው አርሶአደሮች እንደሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት በአከባቢያቸው የነበረው መንገድ በመበላሸቱ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

አሁን በወረዳው እየተከናወነ ባለው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በህብረተሰቡ ተሳትፎ መሠራቱ የነበረውን ችግር እንደሚቀርፍላቸው ተናግረዋል፡፡

በወረዳው ያነጋገርናቸው የቱምትቻ ቀበሌ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ባከናወኗቸው በቡናና በእንሰት እድሳት ሥራ የተገኘውን ውጤት በማየታቸው  በዘንድሮው በተፋሰስ ሥራ በኩታ ገጠም ተደራጅተው እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመንገድ ችግር ወላድ እናቶችን ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ የነበረውን መንገድ ብልሽት ችግር በሳምንት ሦስት ጊዜ  በህብረተሰብ ተሳትፎ ለመፍታት እየሠሩ መሆናቸውንም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል፡፡

የወረዳው  የመንግሥት  ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም በየነ ወቅታዊና በመደበኛ ሥራዎች ላይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ ከገጠር ኮሪደር፣ የህዳሴ ግድብ ሀብት የማሰባሰብ ሥራን ጨምሮ የተፋሰስ ልማት ማከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በተከናወኑ በተፋሰስ ልማት ሥራ የተተከሉ ቡናዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸው በተያዘው ዓመትም በተፋሰስ  5 ሺህ 6 መቶ 69  ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ከታቀደው 6 መቶ 60 ሄክታር መሬት ያረጁ ቡናዎች ነቀላና  7 መቶ ሄክታር በላይ ቡና ጉንደላ በማካሄድ የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታሪኩ ታደሰ በወረዳው በተከናወኑ በተቀናጀ በተፋሰስ ልማት ሥራዎች ከዓመት ዓመት ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቅሰው የቡና ምርታማነት በመጨመሩ በሄክታር ከ18 ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ተናግሯል፡፡

በወረዳው በሚሠሩ የልማት ሥራዎች የህብረተሰብ ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት አቶ ታሪኩ በ2017 ተፋሰስ ልማት ሥራ 10 ኪሎ ሜትር መንገድ በህብረተሰብ ተሳትፎና 10 ኪሎ ሜትር መንገድ በወጣቶች በጎ አገልግሎት መሠራቱን ጠቁመዋል፡፡

በህብረተሰብ ተሳትፎ የተከናወኑ የተለያዩ ፋይዳ ያላቸው የልማት ሥራዎች በገንዘብ ቢተመኑ ከፍተኛ እንደነበር የተናገሩት አስተዳዳሪው የምግብ ዋስትና ችግር ለመቅረፍም በግብርናው የተለያዩ ግብዓት የማቅረብና ድጋፍ የማድረግ ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡

ዘጋቢ፦ እምነት ሽፈራው ከይርጋጨፌ ቅርንጫፍ