እድሜያቸው ከ5 አመት በታች የሆኑ 1.3 ሚሊየን ሕፃናትን በአራት ቀን ዘመቻ የፖሊዮ ክትባትን ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ

እድሜያቸው ከ5 አመት በታች የሆኑ 1.3 ሚሊየን ሕፃናትን በአራት ቀን ዘመቻ የፖሊዮ ክትባትን ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ

በቢሮው የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በ2017 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የተቀናጀ የልጅነት ልምሻ መከላከያ የነፃ ክትባት ዘመቻን በይፋ ጀምሯል።

የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በክልላዊ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተገኝተው ባስተላለፉት መልክት፤ በሕፃናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰውን የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል በሚሰጠው የክትባት ዘመቻ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳሰበዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ የጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አጉኔ አሾሌ፤ በመጀመሪያው ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከ1.3 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ሕፃናት ክትባት ለመስጠት መታቀዱን ገልፀው፤ ለዘመቻው ስኬት ከዘጠኝ ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎችና በጎ መልዕክተኞች ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለዘመቻው ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን ያነሱት አቶ አጉኔ፤ ከአምስት አመት በታች የሆኑ ሕፃናት ያላቸው ወላጆችና አሳዳጊዎች ከዚህ በፊት የፖሊዮ ክትባት ቢከተቡም ባይከተቡም በዘመቻው ወቅት እንዲያስከትቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ከፖሊዮ ዘመቻው ጎን ለጎን የጤና አገልግሎቱን በፍትሀዊነት ተደራሽ ለማድረግ የሕፃናትና የነፍሰጡር እናቶች የሥርዓተ ምግብ ልየታ፣ የቆልማማ እግር ልየታ፣ መደበኛ ክትባት ያልወሰዱና ያቋረጡ ሕፃናትን በመለየት በጊዜያዊ ክትባት መስጫ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

በጂንካ ከተማ በተከናወነው ክልላዊ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ልጆቻቸውን ያስከተቡ ወላጆች ስለክትባት ዘመቻው አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ያላቸውን ሀሳብ አጋርተዋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን