በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በይፋ ተጀመሯል

በክትባት ዘመቻው ከ552 ሺህ በላይ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ተደራሽ እንደሚሆንም ተመላክቷል።

በዕለቱ በታርጫ ከተማ ኢንላይት ህፃናት ትምህርት ቤት የክትባት ዘመቻውን ያስጀመሩት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም እንደገለፁት፤ ማህበራዊ ብልፅግና ማረጋገጥ የሚቻለው የዜጎችን ጤና በመጠበቅ ሲሆን በሽታውን መከላከል የመጀመሪያ ተግባር እና አክሞ ማዳን ደግም ቀጥሎ የሚመጣ ተግባር ነው።

የክትባት ዘመቻ ደግሞ በሽታን ለመከላከል ወሳኝ ተግባር በመሆኑ በሚካሄደው የፖሊዮ ዘመቻ ወላጆች፣ የአካባቢ ነዋሪዎችና የሚመለከታቸው አካላት ህፃናቱ ክትባት እንዲያገኙ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በሽታው በአንድ ቤት ከተከሰት በአካባቢው ሁሉ ሊሰራጭ ስለሚችል በአካባቢው ያሉ ህፃናትን ሁሉ በማስከተብ ወላጆች ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የፖሊዮ በሽታን ከሀገራችን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት የመከላከያ ክትባትን ማስከተብና የአካባቢ ፅዳትንም ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነም አቶ ኢብራሂም አመላክተዋል

በክልሉ ክትባት ዘመቻ 552 ሺህ በላይ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ተደራሽ እንደሚሆኑም አቶ ኢብራሂም አስታውቀዋል፡፡

የዳውሮ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስራት ቸርነት መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ትኩረቱን ባደረገው የጤና ፖሊሲያችን የመከላከያ ክትባት ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም የሚመለከተው አካል በጉዳዩ ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

የአካባቢ ፅዳት ተግባራትን በማጠናከር በሽታውን ለማጥፋት ወሳኝ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እንደሚሻ በመግለፅ በክትባት ዘመቻው ሁሉም ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ተደራሽ እንዲሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል በማለት አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ መካሻ – ከዋካ ጣቢያችን