የስራ ስር ሰብሎች የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ተጠቆመ

በአንጮቴ ሰብል ላይ ያተኮረ የምግብ አውደ ርዕይ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳውላ ካምፓስ ተካሂዷል።

አንጮቴ ከስራስር ሰብሎች አንዱ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ በስፋት ይመረታል።

ከባህር ወለል በላይ ከ1 ሺ 300 አስከ 2 ሺ 800 ሜትር ከፍታ ባላቸው አካባቢዎች እንደሚመረትና በደጋ፣ ወይናደጋና ቆላማ አካባቢዎች በሄክታር ከ150 እስከ 180 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳውላ ካምፓስ የማህበረሰብ ጉድኝትና የቴክኖሎጂ ሽግግር አስተባባሪ አቶ ታደለ ቱባ በመርሀ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ አንጮቴ በዞኑ ደጋ፣ ወይናደጋና ቆላማ የአየር ጸባይ ባለባቸው ሶስት አካባቢዎች የማምረት ሙከራ ተደርጎ በሁሉም የአየር ጸባይ የሚመረት መሆኑን ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።

አንጮቴ የምግብነት ይዘቱ ከሌሎች የስራ ስር ሰብሎች የተሻለና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር የሳውላ ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ተፈራ አሽኔ፤ አንጮቴ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሰብል ሲሆን ህብረተሰቡን የማላመድና የማስተዋወቅ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እንደ አንጮቴ ያሉ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን ተክሎች በማስፋፋት ፋይዳቸውን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር ተባብሮ መስራት ይገባል ብለዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአርባምንጭ ዩኒቨሲሲቲ የሳውላ ካምፓስ የምግብ ምህንድስና መምህርና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ አራርሳ ተሰማ በበኩላቸው፤ አንጮቴ ለማህበረሰቡ በችግሩ ጊዜ የሚደርስና ድርቅን የሚቋቋም፣ በበሽታ የመጠቃት ዕድሉ ያነሰ፣ በትንሽ ስፍራ ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ፣ ከምግብና መድኃኒትነት ባለፈ በርካታ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

የስራ ስር ሰብሎች ለምግብ ዋስትናና ለኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸውን ሚና ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደግፌ በበኩላቸው፤ በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ተክሉን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በማሳቸው ሰብሉን በማምረት ተጠቃሚ ለመሆን መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ከአንጮቴ የሚዘጋጁ ምግቦች ለዕይታ የቀረቡ ሲሆን በአንጮቴ ልማት ላይ ያተኮረ ውይይትም ተካሂዷል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን