ሀዋሳ፡ የካቲት 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የባህል ስፖርቶችና የባህል ፌስቲቫል ውድድር ቱባ የሆኑ ባህላዊ ስፖርቶች ጎልተው የታዩበት ሠላምና አንድነት የተጠናከረበት ውድድር መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ 4ኛው ዙር የባህል ስፖርቶች፣ የባህል ፌስቲቫልና አትሌቲክስ ክልል አቀፍ ውድድር በኮንታ ዞን ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የነበረው ተጠናቋል፡፡
ማጠቃለያው ላይ የተገኙት የስፖርት ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አፈወርቅ ዳና፤ የባህል ስፖርቶች ወንድማማችነትን ያሳየ በመፈቃቀርና በልዩነት ውስጥ ውበትን ያጎናጸፈ በመሆኑ የክልሉ በርካታና ጠቃሚ ዕሴቶች ወጥተው እንዲታዩ ያስቻለ ነው ብለዋል።
የየብሔረሰቡን ጠቃሚ ዕሴቶች በስፖርቱ ዘርፍ በማሳደግ የቱሪስት መስህብና ከዘርፉም የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ይሰራል በማለት ተናግረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አህመዲን አወል በበኩላቸው፤ የብሔሮች ቱባ ባህል ደምቀው የታዩበትና የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር አንደኛው ብሔር ከሌላኛው ጠቃሚ ዕሴቶችን ልምድ በመለዋወጥ ተከባብሮና ተቻችሎ እንዲኖር የሚያስችልና ባህል ጎልቶ የታየበት ነው ብለዋል።
አስራ ስምንት ዓይነት ውድድር የታየበትና የተለያዩ ልምዶች፤ እውቀትና ክህሎት ሽግግር የተገኘበት ውድድር መሆኑ ተመላክቷል።
በቀጣይ ወቅቶችም የብሄሮችን ያልታዩ ጠቃሚ ዕሴቶችን በማውጣት የማስተዋወቅና የገቢ ምንጭ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
በመርሃ-ግብሩ ማጠቃለያ የዞንና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ለባህል ስፖርት ተወዳዳሪዎችና በአትሌቲክሱ ደረጃ ላገኙት የሜዳሊያ ሽልማትና ዋንጫ የተሰጠ ሲሆን ለዝግጅቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች የዕውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቷል።
ዘጋቢ፡ አብዮት እሸቱ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ
ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ገለፀ
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግና ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሀገሪቱ ሰላምን ማስፈን እንደሚገባ ተገለፀ