በማህበር በማደራጀት ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በስልጤ ዞን የወራቤ ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ገለፀ

በተመቻቸላቸው ከወለድ ነፃ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን በከተማው ያነጋገርናቸው አንዳንድ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ተናግረዋል።

በወራቤ ከተማ ካነጋገርናቸው ወጣቶች መካከል የ”ረያን ብሎኬትና ቴራዞን ማምረቻ ማህበር” ሰብሳቢ ወጣት አብድልመጂድ ከማል፤ በ2 ሚሊዮን 5 መቶ ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ብሎኬትና ቴራዞን በማምረት ስራ ተደራጅተን በመስራት ላይ እንገኛለን ብሏል።

ማህበሩ ስራ ከጀመረ አምስት አመት ይሆናል ያለው ሰብሳቢው፤ የቱርክ ማሺኖችን በመጠቀም ጥራት ያላቸውን ምርቶች በማምረት ላይ መሆናቸውን አመላክቷል።

አሁን ላይ የማህበሩ ካፒታል 15 ሚሊዮን ብር መድረሱን በመጠቆም ለማህበሩ የማምረቻ ስፍራ በማመቻቸትና የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ከተማ አስተዳደሩ ምቹ ሁኔታዎችን እንደፈጠረላቸውም ተናግሯል።

ሌላው የ”ጋዛ ጌጣጌጥና የዕደ ጥበብ ውጤቶች ማምረቻ ማህበር” ሰብሳቢ ወጣት አብዱልቃዲር አለማር በበኩሉ፤ ማህበሩ አሁን ላይ ዘጠኝ አባላትን በማሳተፍ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

ማህበሩ የተለያዩ ያገለገሉ እቃዎችን መልሶ በመጠቀም ረከቦት፣ መደርደሪያዎችንና የፕላስቲክ አበባዎችን ጨምሮ ሌሎች የዕደጥበብ ውጤቶችን በማምረት ለገበያ እንደሚያቀርቡ ገልጿል፡፡

ሌላኛዋ ወጣት ዘቢባ ከማል በተመቻቸላት የብድር አገልግሎት ባገኘችው 1 መቶ 50 ሺ ብር “ጠሊል ዲዛይን” በተሰኘ የአልባሳት ማህበር በመደራጀት የተለያዩ የባህል አልባሳትን በመስራት ላይ እንደምትገኝ ገልፃልናለች።

ወጣቶቹ በተፈጠረላቸው የስራ ፈጠራ ዕድል ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውን በመደገፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በ2017 የበጀት ዓመት ከውጭ ሀገር ተመላሾችንና ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ ያልገቡ ዜጎችን በማህበር በማደረጀት ወደ ስራ ለማስገባት ከተማ አስተዳደሩ 14 ሚሊዮን ብር ካፒታል በጀት ዕቅድ በመያዝ እየሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰፋሀዲን ደኑር ገልፀዋል፡፡

በአካባቢው አልፎ አልፎ የሚስተዋለውንና ለማህበራቱ ስራም እንቅፋት የሚሆነውን የመብራት ችግር ለመቅረፍ የትራንስፎርመር ግዢ ለመፈፀም መታቀዱንና ከዚህም ባሻገር ለስራ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዲቻል ሼዶችን በብዛት ለማዘጋጀት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው አብራርተዋል።

ለዘርፉ ውጤታማነት ከወለድ ነፃ የብድር አገልግሎት የተመቻቸ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሰፋሀዲን፤ ከስደት ተመላሾችና ሌሎችም ወጣቶች መንግስት ያመቻቸላቸውን የስራ ፈጠራ ዕድል አጋጣሚን በመጠቀም ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀምና በዚህም ከኢኮኖሚ ጥገኝነት መላቀቅ እንዳለባቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ: ሳሊክ አህመድ – ከሆሳዕና ጣቢያችን