በክልሉ ያሉትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች በተገቢው መጠበቅ እንደሚገባ ተጠቆመ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ከምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የአካባቢ እና ማህበረሰብ ደህንነት ሥራዎች ላይ ያተኮረ ስልጠና ለባለድርሻ አካላት በሚዛን አማን ከተማ ሰጥቷል።

በስልጠና መድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢንጂነር አስራት ገብረማሪያም እንደተናገሩት፤ በክልሉ በአየር ንብረት ጥበቃ ላይ የሚሰሩ በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች መኖራቸውን ጠቁመው ከእዚህም ውስጥ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FSPR) አንዱ ነው ብለዋል።

ስልጠናው በምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ፣ ፕሮጀክቱ እያከናወነ ያለውን ተግባር የመገምገም፣ የመከታተል እንዲሁም የማሳወቅ ስራ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መዘጋጀቱን ነው ዶክተር እንጂነር አስራት ገብረማርያም የተናገሩት።

ፕሮጀክቱ ደኑን መነሻ ያደረጉ ተግባራትን የሚያከናውን በመሆኑ ደኖች እንዳይጎዱና ማህበረሰቡ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ በረጂ ድርጅቶች የሚወርደው በጀት ሥራ ላይ መዋሉን ለመከታተል የስልጠናው ጠቀሜታ የጎላ እንደሆነም ገልጸዋል።

የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናውም በክልል ከሚገኙ ስድስት ዞኖች እና ወረዳዎች የተውጣጡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ተሳታፊዎች በበኩላቸው በአሰራር ሂደት ውስጥ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች አንስተዋል።

በተለይም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት አነስተኛ መሆን፣ የወንዝ ውሃ ብክለት፣ የደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርአት ግንዛቤ ውስንነት መኖር እንዲሁም የአካባቢ ብክለት ላይ የሚታዩ ጉድለቶች መኖር እና ከማእድን ሀብት ጋር ያሉ የተፈጥሮ ሀብትን መልሶ ከማልማት አንጻር ያሉ ውስንነቶች መኖር ሊቀረፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ስልጠናውም ለቀጣይ ስራቸው ስንቅ እንደሚሆናቸው ተናግረዋል።

የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊ እና የአካባቢ ጥበቃ እና አየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደምሴ ደንቦ በበኩላቸው፤ ክልሉ በርካታ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ያለው በመሆኑ ሀብቱን በተገቢው መጠበቅ እና መንከባከብ ይገባል ብለዋል።

በተለይም በክልሉ በርካታ የማእድን ሀብት ያለ እንደመሆኑ መጠን ከማእድን ስራው ጎን ለጎንም መልሶ ማልማት ላይ በትኩረት ማልማትም ያስፈልጋል ብለዋል።

በክልሉ ባሉ ከተሞች የደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገዶች ላይ በተወሰነ ደረጃ የተጀመሩ ጅምር ጥሩ ተግባራት መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ተጠናክሮ መቀጠልም እንዳአለበት ተናግረዋል።

ከቡና ተረፈ ምርት ጋር ተያይዞ መልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች በቡና አብቃይ አካባቢዎች እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ከመስራት አንጻር በተለይም ከጤና፣ ከማዘጋጃ ቤቶች ጋር በከተሞች ተቀናጅተው ከመስራት ባለፈ ህብረተሰቡን በማቀናጀት መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን