በአካባቢው ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲኖር በቀጣይነት እንዲሠራ በኮሬ ዞን የኬሌ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ጠየቁ
“ከቃል እስከ ባህል” ሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ የነዋሪዎች ውይይት መድረክ ተካሂዷል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ በዛብህ ቦጋለ፣ ብርሃኑ ሶያማ እና ሌሎችም እንደተናገሩት፤ በብዙ ፈተናዎች መካከል እንደ ሀገር የህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ የኮሪደር ልማት እና ሌሎች ዘርፎችም ላይ ውጤት መመዝገባቸው አስደሳች ነው።
በህዝብ መረጋጋት ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ቢኖሩም፣ ሕዝቡ የሚረጋጋውና ልማትም የሚመጣው ዘላቂ ሠላም ሲኖር ነው ብለዋል።
እንደኮሬ ዞን ያለው የጸጥታና ሰላም ጉዳይ ትኩረት የሚፈልግ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፤ በግብርና፣ ንግድ፣ የከተማ ልማትና ሌሎች ዘርፎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን አመላክተዋል።
ለዚህም በአካባቢው ሠላምን ለማስፈን የሚሰሩ ተግባራት ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጡ በሚችል መልኩ ቀጣይነት ያለው መሆን አለበት ብለዋል አስተያየት ሰጭዎቹ።
የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ እንደተናገሩት፤ በዞኑ በውጭም ሆነ በውስጥ ያሉ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ ነው ብለው ለውጤታማነቱ በጋራ መቆም ይጠይቃል።
ሠላም የሚጀምረው ከውስጣችን ነው ያሉት አስተዳዳሪው፤ ከአጎራባች ወንድሞች ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውንና ይህ ግን ውጤታማ እንዳይሆን ከመሐል የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሠላም ሐይሎች በመኖራቸው መቀናጀት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
በውይይቱ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ፤ ሕዝቡ ለሠላም እየከፈለ ያለው ዋጋ ከፍተኛ ነው ብለው በክልል በኩል ዘላቂ ሰላም እንዲኖር እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
የሕግ ማስከበሩ ተግባር ታቅዶ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ አብዮት፤ የሚሠሩ ሥራዎችን ከክልሉ ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ግጭትን ማስቀረትና መረጋጋትን መፍጠር የፓርቲው የቀጣይ ትኩረት መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፤ በሁሉም የልማት ሥራዎችም ላይ በውስጥ ያሉንን አቅም ማየት አለብን ብለዋል።
ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የስራ ስር ሰብሎች የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ተጠቆመ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በይፋ ተጀመሯል
በመስኖ ሥራ የተሰማሩ የኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች የተለያዩ ሰብሎችን በጥራትና በብዛት በማምረት የተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡