የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፉት 6 ወራት በርካታ ተግባራት ማከናወን መቻሉን ገለጸ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፉት 6 ወራት በርካታ ተግባራት ማከናወን መቻሉን ገለጸ

ሀዋሳ: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ምክር ቤቱ በህዝብ የተሰጠውን አደራ ለመወጣት በክትትልና ቁጥጥር፣ ህግ በማውጣትና በህዝብ ውክልና ስራዎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ ገለጹ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሔደ ነው።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ፥ በጉባኤው የፀደቁ 13 ደንቦችና አዋጆች ታትመው መሰራጨቱን ጠቁመው፥ 8 የሚሆኑት የትርጉም ስራ ተጠናቆ በህትመት ሂደት ላይ መሆኑን አመላክተዋል።

በቋሚ ኮሚቴዎች በኩል የሚደረገውን መደበኛና ድንገተኛ የአስፈጻሚ አካላት ቁጥጥር እና ግምገማ ተግባራት በእውቀትና ችግር መፍታት የሚችል አቅጣጫ ጠቋሚ እንዲሆኑ በማሰብ ልዩ ልዩ አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት መሰራቱን አፈጉባኤዋ ገልጸዋል።

የማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል፣ የከተሞች ኮሪደር ልማት አፈፃፀምን ለመገምገም፣ የማህበረሰቡን የቆሻሻ አወጋገድና መልሶ የመጠቀም ባህል ምን እንደሚመስል፣ በመነኻሪያዎች ያለው የህዝብ ትራንስፖርት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን፣ የጤና ጣቢያ የማህበረሰብ መድሐኒት ቤቶች አገልግሎትና የመድሐኒት አቅርቦት ችግሮች ተዘዋውረው ምልከታ መደረጉን አስረድተዋል።

በበጀት ዓመቱ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶች ለውጤት እንዲበቁ የሁሉንም አካላት የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅም ዋና አፈጉባኤዋ ጠቅሰዋል።

በማህበራዊ ጉዳዮች በትምህርት ዘርፉ የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው፥ የተማሪዎች መጠነ መቅረት፣ ማርፈድና በመምህራን በኩል የሚስተዋሉ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ያለመሸፈን እና በሌሎችም የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት የትምህርት አሰጣጡ የመስተጓጎል ችግር መቀረፍ ይኖርበታል ብለዋል።

የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ፣ የሴቶች እና ህጻናት መብት አጠባበቅ እና ተጠቃሚነት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ስርዓት ተግባራት በልዩ ትኩረት ሊመራ እንደሚገባም ዋና አፈ ጉባኤዋ አመላክተዋል።

በከተሞች የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን መታገል እንዲሁም የኑሮ ውድነት እና መሰል ችግሮችን ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ተገቢ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

የታዩ መልካም ተሞክሮዎች የበለጠ ለማስፋትና ጉድለቶችን በማረም የህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሊሰራ እንደሚገባ አፈጉባኤዋ አሳስበዋል።

ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ